
ሰቆጣ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ስምንት ወራት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተከናወኑ ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ በአካባቢው ያለው ሰላም በልማቱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም ስምምነት ትምህርት ተቋርጦባቸው በነበሩ 16 ቀበሌዎች ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ተመልሰዋል ብለዋል። አሁንም ችግር ውስጥ ያሉ ቀበሌዎች ቢኖሩም ከችግሩ እንዲወጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ እንደኾነ ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
በ2015/16 የምርት ዘመን የታጣውን ምርት በበጋ መስኖ ለማካካስ 590 ሄክታር በበጋ መስኖ በማልማት ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ ለማግኘት እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡ አሥተዳዳሪው ለመጪው የምርት ዘመን የሚውል ከ69 ሺህ በላይ የማዳበሪያ ግብዓት ተጠይቆ በአንደኛ ዙር 34ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ስለመግባቱም ነው የተናገሩት። ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 4 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማከፋፈል ስለመጀመሩ አብራርተዋል።
በጤናው ዘርፍ በኮሌራ ወረርሽኝ እና በወባ ወረርሽኝ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ቢፈተንም ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ችግሩ ሳይባባስ መቋቋም እንደተቻለም ነው የገለጹት፡፡ አቶ ኃይሉ በጤና መድኅን በኩልም የእቅዱን 71 በመቶ በማከናወን እስከመጋቢት 30/2016 ዓ.ም ድረስ ቀሪውን ለማሳካት እየሠሩ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡
ከድርቁ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ የሰጡት ዋና አሥተዳዳሪው በድርቁ ምክንያት ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከመንግሥት እና ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች 51ሺህ 186 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ ስለመደረጉ ነው የገለጹት፡፡ በድጋፉም 360 ሺህ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ስለመቻሉ ነው ያብራሩት።
በገንዘብ ደረጃም 268 ሚሊዮን 639ሺህ 388 ብር ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ ይህም ለ207ሺህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ማከፋፈል እንደተቻለ ገልጸዋል። ስለተደረገው ድጋፍ ምሥጋና ያቀረቡት አቶ ኃይሉ በቀጣይም ከ444 ሺህ በላይ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርን ለማልማት ቁርጠኛ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በመንገድ ዘርፍ በክልሉ በጀት ከ293ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል። ለአራት ዓመታት የመልካም አሥተዳደር ችግር ኾኖ የቆየው የስሃላ ሰየምት ወረዳን ከዞኑ ጋር የሚያገናኘው የተከዜ ድልድይ ከተጀመረ ሁለተኛ ወሩ ላይ ቢኾንም በክልሉ መንግሥት ድጋፍ እና ክትትል የድልድዩ ሥራ 60 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም የተፈቀዱት አራት የአስፖልት መንገድ ሥራዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሕዝቡን የመልማት ጥያቄዎች በመለየት ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል ያሉት አቶ ኃይሉ የልማት እና የሰላም ጸር የኾነውን ጽንፈኛ ቡድን በመከላከል የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። የዋግ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ያሳየውን የሰላም ዘብነት ካስቀጠለ መንግሥት በየደረጃው ያሉ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!