የዳንግላ ከተማ ነዋሪዎች ዘላቂ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ ከሠራዊቱ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ አረጋገጡ።

19

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዳንግላ ከተማ ነዋሪዎች ከጎጃም ኮማንድፖስት አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት ፣ “ፅንፈኛው ምንም ዓላማ የሌለው እና የግል ጥቅሙን የሚያግበሰብስ በመሆኑ ንብረታችንን ይዘርፋል፣ የገንዘብ መዋጮ በየጊዜው አስገድዶ ይሰበስባል፤ ሕዝቡ የልማት ሥራ እንዳይሠራ እያደረገ ይገኛል ስለዚህ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰላማችን ለማረጋጋጥ እንሠራለን” ብለዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኘው ክፍለጦር ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሌተናል ኮሎኔል ገብረኪዳን ሀድጉ “ፅንፈኛው ቡድን ለአማራ ሕዝብ ምንም ዓይነት ጥቅም የሌለው እና የክልሉን መሰረተ ልማት ወደ ኋላ የሚጎትት፣ ህፃናትና ወጣቶች ተምረው ቤተሰባቸውን እና ማህበረሰቡን እንዳይለውጡ በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ለጥፋት አላማው ማስፈፀሚያ በመጠለያነት እየተጠቀመበት ይገኛል” ብለዋል፡፡

ሠራዊቱ ከክልሉ ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ፅንፈኛውን ቡድን ከሕዝቡ ነጥሎ እርምጃ የመውሰድና ለሕግ የማቅረብ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በዚህም ሰላም ወዳድ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለሠራዊቱ በሚሰጡት ጥቆማ በርካታ የፅንፈኛ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለናል ብለዋል ።

ሠራዊቱ የሕዝቡን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ ግዳጁ የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመክፈል የፅንፈኛን ቡድን ከሕዝቡ ነጥሎ እርምጃ የመውሰድና ለሕግ የማቅረብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። መረጃዉ የጎጃም ኮማንድፖስት ነዉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ኀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ይገባል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮምፕሊያንስ ቀንን እያከበረ ነው።