
ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት ከከተማ አሥተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ አባላት እና ከቀበሌ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ኅብረተሰቡ የእለት ከእለት ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታትም ኅብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው ያለ መሪ የሰላም ባለቤት ኾኖ በተሰማራበት የሥራ መስክ በቅንነት ማገልገል ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ሕዝቡም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ አለበት ነው ያሉት፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ያምራል ታደሰ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መነጋገርን በማስቀደም በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ያሳሰቡት፡፡ በቁርጠኝነት በመሥራት ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ቤተልሄም አሰፋ ናቸው፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ እና አቅም ግንባታ ኀላፊ አበባው ግዛቸው አመራሩ እና አባላቱ ግንባር ቀደም ኾነው በመገኘት ሕዝብ እና መንግሥት የጣለባቸውን ኀላፊነት በቁርጠኘነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እና ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘበናይ ዳኛቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!