በዓለም ላይ የሚገኙ ሀገራት ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የተለያየ አሠራር ይከተላሉ።

36

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአንዳንድ ሀገሮች በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን የያዘው የፖለቲካ ፓርቲ ለመረጠው ሕዝብ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና መራጩ ሕዝብ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ የፓርላማ እና የመንግሥት የካቢኔ አባላትን ብቻ ይመዘግባሉ። ለዚህ ደግሞ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን እና ኖርዌይ ተጠቃሾች ናቸው።

አንዳንድ ሀገሮች ደግሞ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ብቻ ይመዘግባሉ። ይህ የሚመረጥበት ምክንያት የፖለቲካ ተመራጮች፣ ከፍተኛ ሚኒስትሮች እና ቁልፍ የኾኑ የተቋማት ኀላፊዎች በፖሊሲ ማርቀቅ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ስላላቸው ነው፡፡ አርመኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ኮሶቮ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።

“ኀላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው በግል ጥቅም ተጽዕኖ ሥር የመውደቅ እድል ያላቸው ከፍተኛ የፖለቲካ ባለስልጣናት ብቻ ሳይኾኑ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችም ጭምር ናቸው” ብለው የሚያምኑ እንደ ቤላሩስ፣ ላቲቪያ እና ፖላንድ የመሳሰሉ ሀገሮች ደግሞ ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኛ ሃብት እና የገቢ ምንጭ ይመዘግባሉ።

በኢትዮጵያም ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የሕዝብ ተመራጮችን፣ ተሿሚዎችን እና የሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ሃብት እና የገቢ ምንጭ እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ በአማራ ክልልም የሕዝብ ተመራጮች፣ ተሿሚዎች እና ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ የተጣለባቸው የመንግሥት ሠራተኞች ሃብት እና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያስመዘግቡ በአዋጅ ቁጥር 187/2003 መቀመጡን የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የሃብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተር ይልቃል ወርቅነህ ነግረውናል።

የሃብት ምዝገባውን ከተሾሙ፣ ከተመረጡ ወይንም ከተቀጠሩ በ45 ቀናት ውስጥ የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለባቸው አዋጁ ያስቀምጣል። የመጀመሪያ ምዝገባ ከተደረገ ከ2 ዓመት ተኩል በኋላ ደግሞ እድሳት ማድረግ አለባቸው። ሃብት አስመዝጋቢዎች በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ እስከቀጠሉ ድረስ በየ2 ዓመት ተኩል ሃብት እና የገቢ ምንጫቸውን የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ነግረውናል።

➽. ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ አሳማኝ ባልኾኑ ምክንያቶች ያላስመዘገቡ እንደኾነ 1 ሺህ ብር መቀጫ ከፍለው በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል፡፡

➽. በመደበኛ ወይም በተራዘመላቸው የማስመዝገቢያ ጊዜ ሃብታቸውን ካላስመዘገቡ ወይም ኾን ብሎ ትክክል ያልኾነ የምዝገባ መረጃ የሰጡ እንደኾነ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 417/2 በተደነገገው መሠረት እስከ አምስት ዓመት እሥራት ያስቀጣል፡፡

➽. ከዚህ በተጨማሪ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 419/2 ያልተመዘገበ ማናቸውም ሃብት ማስረጃ ካልቀረበበት በስተቀር ምንጩ እንዳልታወቀ ንብረት ይቆጠራል፡፡ በሙስና ወንጀል አዋጅ መሠረት ንብረቱ ይወረሳል፤ በእሥራትም ያስቀጣል፡፡

በአማራ ክልል ሃብት መመዝገብ ከተጀመረ ከ2005 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም 150 ሺህ 491 ሰዎች ሃብታቸውን አስመዝግበዋል። ከዚህ ውስጥ 886 ተመራጮች፣ 25 ሺህ 902 ተሿሚዎች እና 123 ሺህ 703 የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው።

በሌላ በኩል ከአጠቃላይ ከአስመዘገቡት ውስጥ 103 ሺህ 685 የመጀመሪያ፣ 46 ሺህ 394 እድሳት፣ 412 ደግሞ በአገልግሎት ማቋራጥ ያስመዘገቡ ናቸው። በ2016 ዓ.ም በክልሉ በተከሰተው የሰላም ችግር በታቀደው ልክ መመዝገብ አለመቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከሃብት ምዝገባ ባለፈ በሚቀርብለት ጥቆማ እና ለሙስና ተጋላጭ በኾኑ መሥሪያ ቤቶች ላይ የአስመዝጋቢዎችን የሃብት ትክክለኛነት የማጣራት እና የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። የሃብት ማረጋገጥ ሥራ ከተጀመረበት ከ2012 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ. ም ባለው ጊዜ በ371 ሰዎች ላይ የማረጋገጥ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ 99 ሰዎች ሃብታቸውን በትክክል አስመዝግበው ተገኝተዋል፤ 166 ሰዎች ጥቃቅን ስህተት ፈጽመው በመገኘታቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፤ 106 ሰዎች ደግሞ ሃብታቸውን ሰውረው በመገኘታቸው ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ መላኩን ገልጸዋል። በቀጣይ ከመመዝገብ ባለፈ የሃብት ማረጋገጥ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከዕለታዊ ጥቅም የተሻገረው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ!
Next articleበጎጃም ኮማንድፖስት የተሰማራው ኮር በሰሜን ጎጃም ዞን እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቀጠና 57 የጽንፈኛውን አባላት መደምሰሱን አስታወቀ።