
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 9 ሺህ 60 ተፋሰሶችን ለመሥራት ታቅዷል፡፡ ሥራው 376 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተሠራ ሥራ በርካታ ተፋሰሶች አገግመው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው፡፡
አርሶ አደር ሙሐመድ ይማም ይባላሉ፡፡ በአርጎባ ልዩ ወረዳ 01 ፈጠቆማ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ሙሐመድ በየዓመቱ በተሠራ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ አካባቢያቸው ከቦረቦርነት ወጥቶ በተለያዩ የቆላ ፍራፍሬዎች ተሸፍኗል፡፡
ከተፋሰሱ በታች በኾነው የእርሻ መሬታቸው ላይ የተለያዩ የቆላ ፍራፍሬዎችን ተክለዋል፡፡ በሥሩም ሽንኩርት እና ቲማቲም ያመርታሉ፡፡ በዚህም በየቀኑ ገቢ አላቸው፡፡ አርሶ አደር ሙሐመድ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራው ባልተጠናከረበት ወቅት መሬቱ በጎርፍ የተጋጋጠ በመኾኑ ማሣቸው ከምርት ሊወጣ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
አሁን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራውን በፍላጎት እንደሚሠሩት ነው የነገሩን፡፡ አርሶ አደር ሙሐመድ ኑሮአቸው ተሻሽሏል፤ በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን አስተምረው ለውጤት አብቅተዋል፡፡“ዛሬ በአርጎባ ልዩ ወረዳ 01 ፈጠቆማ ቀበሌ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ማምረት አይታሰብም” ብለዋል፡፡ ልጆቻችን አልባሌ ቦታ ከመዋል ተቆጥበዋል፡፡
አርሶ አደሩ በሠራነው ልክ እያገኘን ነው ይላሉ፡፡ የዚህን ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራን ያለማንም ቀስቃሽ ሠርተው እንዳጠናቀቁም አርሶ አደር ሙሐመድ ነግረውናል፡፡ አርሶ አደር ሙሐመድ “ዛሬ የቀን ገቢ አለን፣ የሳምንት ገቢ አለን፣ ወርሃዊ ገቢም በቋሚነት እያገኘን ነው” ብለዋል፡፡
ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ኢብራሂም ሀሰን ይባላሉ፡፡ የመዲና ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ በየዓመቱ በፍላጎታቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ እንደሚሠሩ ነግረውናል፡፡ በአካባቢያቸው የተሠራው እና ያገገመው “የደለመኒ ተፋሰስ” ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ለወጣቶችም ተስፋ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ ችግኞችን እያለሙ ተጠቃሚ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ መሬታቸው በጎርፍ ከመጠቃት እንደዳነ እና የተሻለ ምርት እየሠጠ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ወንዞች አልደረቁም፤ ችግኞቻችን በቂ ውኃ እያገኙ ነው፡፡ በቀበሌያችን እስካሁን ያልተጀመረ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዚህ ዓመት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
የአርጎባ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም እንድሪስ በወረዳው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ሥራው ወደ መሬት መውረዱን ተናግረዋል፡፡ በወረዳው የጠረዼዛ እርከን ከሁሉም ተመራጭ ሥራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በወረዳው 1 ሺህ 340 በላይ ወጣቶች በተሠሩ ተፋሰሶች ላይ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የቆላ ፍራፍሬ እያመረቱ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 89 ወጣቶች “ደለመኔ ተፋሰስ” ላይ እንደሚሳተፉም ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ ከመደበኛው ቀን ባሻገር በንቅናቄ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ አሁን መቀስቀስ ቀርቷል የሚሉት ኀላፊው ሁሉም ለራሱ ገቢ ሲል ሥራውን በፍላጎት እንደሚሠራው ተናግረዋል፡፡ ከቋሚ ፍራፍሬ በተጨማሪ አትክልት እየተመረተ ለገበያ እየቀበ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ የዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ 102 በመቶ እንደተጠናቀቀም ተናግረዋል፡፡ ወጣቶችን ለገቢ ያበቃ ይህ ሥፍራ የጠረዼዛ እርከን ልዩ መለያችን እስኪኾን ድረስ እንሠራለን ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ማዕከል እንዲያደርጉትም እየሠሩ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ቡድን መሪ መገርሳ ተሾመ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የዞናችን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አቶ መገርሳ የዞኑ 90 በመቶ የመሬት አቀማመጥ ተዳፋት እና ለአፈር ክለት የተጋለጠ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የሚሠራው የተፋሰስ ሥራ ድንበር ተሻጋሪ ነው ያሉት ቡድን መሪው 82 በመቶ የሚኾነው የተፋሰሱ ክፍል ወደ ዓባይ ሸለቆ የሚፈስ ሲኾን 18 በመቶ ወደ አዋሽ ተፋሰስ የሚሄድ በመኾኑ የታላቁን የህዳሴ ግድብ በመታደግ በኩል ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ 2 ሺህ 778 ተፋሰሶች አሳታፊ እና የተቀናጀ እቅድ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ሥራ የገቡ ሲኾን እስካሁን 94 በመቶ ያክሉ ተጠናቅቀዋል ነው ያሉት፡፡ ቀሪዎቹን ለማጠናቀቅም እንሠራለን ነው ያሉት ኀላፊው የአፈር ክለቱ ሙሉ በሙሉ እስኪቀረፍ ድረስ አጠናክረን እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ በሥራው ላይ 355 ሺህ 830 በላይ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲኾን 28 ሺህ 865 ሄክታር መሬት መሸፈን መቻሉን አንስተዋል፡፡
አርሶ አደሮች የድካማቸወን ውጤት እንዲያገኙ ሥራው አንደተጠናቀቀ የተፋሰስ ኅብርት ሥራ ማኅበራትን በማቋቋም ከአርሶ አደሮች ጋር ርክክብ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ እስከ ዛሬ የነበሩ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ወደ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች ኅብርት ሥራ ማኅበር የማሸጋገር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ 9 ሺህ 60 ተፋሰሶች ለመሥራት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡ ሥራው 376 ሺህ 99 ሄክታር መሬት ይሸፍናል ብለዋል፡፡ እስካሁንም 127 ወረዳዎች 4 ሺህ 361 ተፋሰሶች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ እስከ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም ድረስ በተሠራ ሥራ 105 ሺህ 530 ሄክታር በላይ መሬት እንደተሸፈነ ተናግረዋል፡፡ 28 ሚሊዮን 338 ሺህ 430 ሰዎችም በተደጋጋሚ ተሳታፊ ኾነዋል፡፡
ከሚሠሩ ስትራክቸሮች ውስጥ የማሣ ላይ እርከን፣ የጠረዼዛ እርከን፣ የተራራ ላይ ስትራክቸሮች፣ አነስተኛ የውኃ ስትራክቸሮች፣ ቦረቦርን ማዳን እንዲኹም የተሠሩ ተፋሰሶችን ደረጃ የማሳደግ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት አቶ እስመለዓለም፡፡ በየአካባቢው የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በመቋቋማቸው የባለቤትነት ሥሜት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ተፋሰሶች ጉዳት ሳይደርስባቸው መቅረታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተፋሰሶችን ዘላቂ ለማድረግ ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ማጠናከር አንዱ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ባለፈው ዓመት በተሠሩ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡
የተፋሰሶችን ዘላቂነትን በማስጠበቅ በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡ለማገዶ እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የደን ውጤቶች በብዛት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ እስመለዓለም ምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ላይ በተወሰደ ናሙና የተሻለ ቁጥር ያላቸው ችግኞች የጸደቁ ቢኾንም ምዕራብ አማራ አካባቢ እንዳልተገመገመ ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራው በጥር ወር የተጀመረ ቢኾንም ባለው ሀገራዊ ጉዳይ የተነሳ ሥራውን ያልጀመሩ ወረዳዎች አሉ፤ የጀመሩትም በወቅቱ አለማጠናቀቃቸውን ገልጸው እስከ ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም ድርስ አንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው ያሉት ኀላፊው በቀሪ ቀናት የተሻለ ሥራ በመሥራት እቅዱን ለማሳካት ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ የተሠራባቸው አካባቢዎች ድርቁን መቋቋም እንደቻሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ ሁሉም በዚህ ልክ እንዲሠራ እና ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል፡፡ የተፋሰሶችን ዘላቂነት ለማስቀጠል የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለቸውም መክረዋል፡፡ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ሥልጠና የወሰዱ ቀያሽ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው ያለውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራን መሥራት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ መክረዋል፡፡
በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ተመራማሪ ኃይሉ ክንዴ (ዶ.ር) የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የአፈር ክለትን ከመከላከል ጎን ለጎን ጎርፍ ኾኖ የሚሄደውን ውኃ በማስረግ ወንዞች ዓመቱን ሙሉ ጥቅም እንዲሠጡ ያደርጋል ብለዋል። በአፈር ውስጥ የሚኖረው የውኃ መጠን ከጨመረ የምንተክላቸው ችግኞች ብሎም በመስኖ የሚለሙ ሰብሎች እና ቋሚ ተክሎች በቂ ውኃ እንዲያገኙ እና የታለመውን ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳል ብለዋል።
ዶክተር ኃይሉ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአፈር ክለት ምክንያት የምግብ ዋጋ በየዓመቱ ከ3 ነጥብ 5 እስከ 4 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መኾኑን ጠቁመዋል። የአፈር ክለትን በመጨር የውኃ ስርገትን ከፍ ማድረግ ከተቻለ ወንዞች የተሻለ ፍሰት ሥለሚኖራቸው ከመኸር ባሻገር የመስኖ ምርታማነት ይጨምራል። ለመስኖ ብሎም ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የምንሠራቸው ግድቦች ተገቢውን የውኃ መጠን እንዲያገኙ እና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሠጡ ያስችላልም ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ በበጋ ከሚሠራው የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራው ባሻገር በክረምት የሚተከሉ ደኖችን ስለሚጨምር ሥራውን አቀናጅቶ መሠራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዶክተር ኃይሉ በበጋ የምንሠራው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በክረምት ለሚተከሉ ችግኞች መሠረት ነው። ክልሉ ከእርከን ሥራ ባሻገር በክረምት የሚተከሉ ችግኞችን እያለማ ነው ይህም ሥራውን ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።
ሌላው በካርቦሃይድሬት መጨመር የሚፈጠረውን የዓለም ሙቀት መጨመር ለመከላከል ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል። የዓለም ሙቀት መጨመር ያልተመጣጠነ የዝናብ ሥርጭት እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል። ዝናቡ በአንድ ጊዜ ዘንቦ ጎርፍ በመኾን ችግር የሚፈጥርም ይኾናል። ይህ እንዳይከሰት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
ተመጋጋቢ የኾነ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ተመራማሪው በየዓመቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሥራው ላይ እየተሳተፉ እንደኾነም ጠቁመዋል። ከ2003 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም በተሠራ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ በሄክታር ሁለት ቶን ወይም 20 ኩንታል አፈር ማስቀረት መቻሉን ነው የገለጹት።
በክልሉ ባለፉት 30 ዓመታት በተሠሩ ትልልቅ የመስኖ ግድቦች ውስጥ 10 በላይ የመስኖ ግድቦች በአፈር ደለል ተሞልተው ከጥቅም ውጭ መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ጥናት እንደሚያሳየው የአፈር ክለት በሄክታር ከአምስት ቶን ከበለጠ አደጋ ነው ይበል እንጅ እንደ አማራ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ የአፈር ክለቱ 20 ቶን በሄክታር ነው። ይህን ለማስተካከል በየዓመቱ የሚሠራውን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ በእጥፍ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሚሠሩ ልማቶች ከጥቅም ውጭ ይኾናሉ ነው ያሉት። አርሶ አደሮች ባለሙያዎች መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ይህን አውቀው መንቀሳቀስ ካልቻሉ ችግሩ ወደኋላ ሊመለስ ይችላል ብለዋል።
በ2003 ዓ.ም በክልሉ የነበረው የአፈር ክለት መጠን 22 ቶን በሄክታር ነበር ያሉት ተመራማሪው፣ በ2014 ዓ.ም 20 ቶን በሄክታር ደርሷል። በ11 ዓመት ውስጥ 2ቶን ብቻ ከቀነስን ከዓለም አቀፉ ስታንዳርድ ለመድረስ 50 ዓመት ይፈጃል። ስለዚህ ይህ እንዳይኾን ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!