
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዞናዊ ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው፡፡ ኮንፈረንሱ የመሪዎችን አንድነት በማጠናከር የሕዝብን የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ያስችላል ነው የተባለው፡፡
ውይይቱ የአካባቢውን አሁናዊ ሁኔታ በውል በመረዳት ሰላምን ለማስፈን እንደሚረዳ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ ግጭት እርሰ በእርስ ከመጨራረስ ውጭ ምንም ዓይነት ጠቃሜታ እንደሌለው ባለፉት ወራት ተምረናል ብለዋል፡፡ ለሁሉም ነገር ሰላም ያስፈልጋል፣ ጥያቄ እንኳን መነሳት ካለበት ሰላማዊ እና ሕጋዊ በኾነ መንገድ መነሳት አለበት ነው ያሉት፡፡
የኃይል አማራጮችን መጠቀም ከጉዳት ውጭ ጥቅም እንደሌለው ነው ያመላከቱት፡፡ ለሰላም በተሠራው ሥራ በአካባቢው አንጻራዊ መረጋጋት መምጣቱንም አንስተዋል፡፡ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የግጭትን አስከፊነት በመረዳት ለሰላም እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም የሕሊና ዕረፍት መኾኑን መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በየደረጃው በተካሄዱ ውይይቶች ማኅበረሰቡ ሰላም እንደሚፈልግ አስታውቋልም ብለዋል፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳኛቸው ፈንታሁን በፓርቲው የአሠራር ሥርዓት መሠረት እተካሄደ የሚገኝ ኮንፈረስ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ኮንፈረንሱ ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም አሁን ያለውን ችግር ለማረም እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
የነበሩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልም እንደሚያግዝ ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይ ዓመታትም በተሻለ እቅድ፣ በአንድነት እና በተነሳሽነት ለመሥራት ይረዳል ብለዋል፡፡
አሁናዊ ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችል የጋራ አመላከከት እና የተግባር አንድነት እንዲኖር የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የነበረው የፀጥታ ችግር ሰፊ መሻሻል እያሳየ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በዞኑ መሪዎች፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ከሕግ ማስከበር ሥራው ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ ሰላም የሚመጣው በጋራ ጥረት ነው ያሉት ኀላፊው ኮንፈረንሱ ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡
ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡ የፓርቲ መሪዎች ከፓርቲው ዓላማ እና ተልዕኮ ተነስተው የሚጠበቅባቸውን የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት በመፍጠር ከፀጥታ ችግር በመውጣት የተሻለ አካባቢ መፍጠር የኮንፈርሱ ዓላማ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ፓርቲ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የብልጽና ፓርቲ ግጭቶችን ለመፍታት የሰጣቸው ሰላማዊ አማራጮች በዞኑ ለውጥ እያመጡ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ በዞኑ ከፍተኛ ሰበዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱንም አስታውቀዋል፡፡ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ኮንፈረንሱ ፓርቲው ባለፉት ጊዜያት ያከናወናቸውን የልማት፣ የሰላም፣ የመልካም አሥተዳደር እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አፈጻጸም የሚገመግም እና አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ለሕዝብ ቃል በገባቸው የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር፣ የሰላም፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሂደትም የአፈጻጸም ችግር ያላባቸውን በተገቢው መንገድ መክሮ ሕዝብን በመያዝ አፈጻጸሙን የተሻለ ለማድረግ ያለመ ኮንፈረንስ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ክልሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ መኾኑን ያነሱት አቶ ሲሳይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል እና የፖለቲካ መሪዎች ከአርቆ አሳቢው ሕዝብ ጋር በመተባበር በተሠራው ሥራ አንጻራዊ ሰላም መጥቷል ብለዋል፡፡ አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ከፀጥታ ችግር ነጻ እየኾነ የሕግ የበላይነት እየተረጋገጠ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ኮንፈረንሱ የእስካሁኖቹን ሥራዎች በመገምገም ቀሪ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚመክር ነው ብለዋል፡፡ የተጀመረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በማሸጋገር የሕዝብን ጥያቄ ለማስመለስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በኮንፈረንሱ የሚሳተፉ አካላት የተጀመረውን አንጻራዊ ሰላም በማስፋት ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሸጋገር እንዲያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ አቶ ሲሳይ “ኮንፈረንሱ የእስካሁኖቹን ሥራዎች በመገምገም ቀሪ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚመክር ነው” ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!