
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኅብረት ሥራ ማኅበራት የኅብረተሰቡን ችግር በማቃለል የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመኾኑ በተለያየ ዓይነት እና ደረጃ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚጠቀሱ ሲኾን ለአባሎቻቸው እና ለቀሪው የኅብረተሰብ ክፍል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበር ማደራጃ እና ማስፋፊያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ባዩ ከበደ በዞኑ 39 የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና አራት ዩኒየኖች መኖራቸውን ተናግረዋል። ማኅበራቱ የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል ኀላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡
አባል የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከመሸመት ባለፈ የተለያዩ የቁጠባ እና የብድር አገልግሎትም ተጠቃሚ እንደኾኑም አስረድተዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች በሦስት ወር ክፍያ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የካፒታል እጥረት እና የመዋቅር ችግሮች ተቀርፈውላቸው በሙሉ አቅም እንዲያገለግሉ ለማስቻል የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች መጀመራቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።
በንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ማኅበራቱን ለማጠናከር ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ማኅበራቱን መደገፍ ተችሏል ተብሏል ።
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!