
ደሴ: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ስምንት ወራት ከሰላም እና ደኅንነት ተግባር ባሻገር የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በተሻለ መንገድ መፈጸማቸውን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተናግረዋል፡፡ የደሴ ከተማ እና አካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ዳር ለማድረስ እየተሠራ መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል።
አቶ ሳሙኤል በሰጡት መግለጫ የደሴ ከተማን በቀጣናው ካሉ ከተሞች ጋር በልማት በማስተሳሰር ለማዘመን እና ገጽታዋን ለመቀየር የከተማ አሥተዳደሩ ጠንክሮ እየሠራ ነው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የሚገነቡት የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የመናሐሪያ፣ የድልድይ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የከተማዋ የረጅም ጊዜ የመልማት ጥያቄዎች እንደነበሩ ነው ያብራሩት፡፡
በልማቱ የከተማዋን ማኅበረሰብ ተሳታፊ በማድረግ የዘመናት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ማኅበረሰቡ እያከናወነ ላለው ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የከንቲባ ችሎት በማቋቋም የዜጎችን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በመፍታት ላይ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም ችግር በከተማዋ በሚሠሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ላይ ጫና እያሳደረ መኾኑንም ጠቁመዋል። በጽንፈኛ ኀይሉ የተከሰተው የሰላም እና ጸጥታ ችግር በከተማዋ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት እንዲስተጓጎል ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
መንገድ በመዘጋቱ አዲስ አበባ የተገዛ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ 1 ሺህ 400 ኩንታል ስኳር እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማምጣት አልተቻለም ብለዋል። በዚህም ሕዝቡን ለኑሮ ውድነት ዳርጓል ነው ያሉት፡፡ ዘንድሮ ከ30 እስከ 50 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። ይሄን ተግባር በተሳካ ኹኔታ ለመፈጸም ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ትብብሩን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!