
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግርን መትከል” በሚል መሪ መልዕክት የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የዞኑ አመራሮች እና የመንግሥት ሠራተኞች በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩም የአማራ ክልል ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ተገኝተዋል። ሰላም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ዋነኛ ምክንያት ነው ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች ሰላምን ለማስቀጠል በዞኑ ካለው የፀጥታ መዋቅር ጋር በጥምረት እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
የዞኑ ሕዝብ ባለፈው የአገዛዝ ሥርዓት የደረሰበት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በርካታ መኾኑን አንስተው መንግሥት በደል የደረሰበትን ሕዝብ ችግሮች በመመልከት መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ሰላምን በማስጠበቅ በጦርነት ወቅት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በማይነጥፈው የሕዝብ ድጋፍ በመገንባት ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በትብብር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
መንግሥት በዘላቂነት የማንነት ጥያቄያቸውን በመመለስ አማራዊ ማንነታቸውን እንዲያጸናላቸው ነው ያሳሰቡት። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ የጎንደር በጌምድር አማራ ለመኾኑ ብዙ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ ያሉት የዞኑ አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የእውነት የማንነት ጥያቄ ትግል መቸም አይሸነፍም ብለዋል።
ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ ሰላምን እና ኅብረ ብሔራዊነትን በማስቀጠል የዘመናት ጥያቄያቄዎች እውን እንዲኾኑ ሁሉም በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ አማራ ለመኾኑ ከሰዎች ምስክርነት ባለፈ እንደ ጎንደር ቤተ መንግሥት የታነፀው የአያና እግዚ ቤተ መንግሥት ምስክር ነው ብለዋል።
ወጉ፣ ባሕሉ እና ማንነቱም አማራ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው ለሰላም ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ አሁን ላይ ዞኑ ላለበት ፍፁም ሰላምም የፀጥታ አካሉ እና የአመራሩ ሚና የላቀ መኾኑን ጠቁመው ለዚህም ሥራ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!