”ሀገርን ማፍረስ፣ ሥልጣንን በጉልበት መቀማት የማይቻልበት ሀገር እና ክልል መኾናችንን አሳይተናል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

102

ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ”ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት ኮንፈረንስ አካሂዷል። በኮንፈረንሱ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል በከተማ አሥተዳደሩ፣ በአማራ ክልል እና በኢትዮጵያ የተሠሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ሪፖርት ለውይይት ቀርቧል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ኮንፈረንሱ ብልጽግና ፓርቲ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ የሠራቸውን እና የቀጣይ ጊዜ ሥራዎችን የሚለይበት መኾኑን ተናግረዋል። ፓርቲው ፈተናዎች ሳይበግሩት ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እየፈጸመ እና የለውጥ ጉዞን በመምራት ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል። ከውስጥም ከውጪም ኾነው ሀገር ለማፍረስ የሚያሴሩ ኀይሎችን ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ያጋጠመው ፈተና የብልጽግናን የለውጥ ጉዞ የሚጎዳ እንደነበረ እና በፓርቲው፣ በመንግሥት እና በሕዝቡ አስተዋይነት ሀገርን ከመፍረስ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። ”በአሁኑ ሁኔታ ሀገርን ማፍረስ፣ ሥልጣንን በጉልበት መቀማት የማይቻልበት ሀገር እና ክልል መኾናችንን አሳይተናል” ብለዋል።

በሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ኮንፈረንስ በመመካከር ሰላምና ልማትን የበለጠ ማረጋገጥ የምንችልበት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ልማትን በማስቀጠል፤ ከተማን ጽዱ፣ ውብ እና ማራኪ በማድረግ ለነዋሪዎቿም፣ ለእንግዶቿም የምትመች እና የምትናፈቅ ለማድረግ ሥራ ስለመጀመሩ ነው የገለጹት።

ከንቲባው ”ሰላማችን እየጠበቅን ሕዝቡን ወደ ጉስቁልና ለማውረድ የሚፈልጉ ኀይሎች ተስፋ እንዲቆርጡ ያደረግንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን” ነው ያሉት። ”ጽንፈኛ ኀይሎች አጥፊ፤ ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጡ ናቸው፤ እነዚህ ኀይሎች በድጋሚ መሰል ስህተት እንዳይሠሩ በአስተሳሰብም ደረጃ ከሕዝብ ጋር የምንግባባበትን ሁኔታ አስበን ይህን ኮንፈረንስ እያካሄድን ነው” ብለዋል።

ያልተሠሩ ሥራዎችን በፍጥነት በመምራት ብልጽግናን ማረጋገጥ ከአባላቱ የሚጠበቅ መኾኑን የተናገሩት ከንቲባ ጎሹ አባላት በቀጣይ ሳያወላውሉ ለአንድ ዓላማ መሰለፍ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። ትልቁ የልማት አቅም ሕዝብን ማንቀሳቀስ ነው፤ ተመራጭ ከተማ ለማድረግም በመደጋገፍ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን ፓርቲው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ለውጦችን አንግቦ የተነሳ እና በርካታ ለውጦች ያስመዘገበ መኾኑን ገልጸዋል። ችግሮችን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባሳተፈ እና አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጦ በትጋት እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ለውጡን በድል ለማስቀጠል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።

አቶ ሞላ ”ፓርቲያችን እና መንግሥታችን በሰጡት ቁርጠኛ አመራር፤ በመከላከያና በጸጥታ ኀይሎች ተጋድሎ እንዲሁም በአስተዋዩ ሕዝብ ትብብር በጽንፈኝነት ምክንያት ተጋርጦብን የነበረውን የመፍረስ አደጋ መዳን ችለናል” ብለዋል። በከተማ እና በክልሉ የተፈጠረው የጽንፈኝነት አደጋ፣ የሀገር ውስጥ አለመረጋጋት፣ ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት እና የገቢ አሠባሠብ፣ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥ መጨመር፣ ዓለም አቀፋዊ የገበያ አለመረጋጋት እና ደካማ የመፈጸም አቅም ወደፊት መስተካከል ያለባቸው ስለመኾናቸው አንስተዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ወጣት ወርቁ ምንይበል ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ ቅስቀሳ ቃል የገባቸውን ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል ብሏል። በዚህም የማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሥራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን ጠቅሶ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የበለጠ መሥራትን እንደሚጠይቅ ገልጿል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የኮንፈረንሱ ተጋባዥ ተሳታፊ አቶ ያየህይራድ በለጠ ብልጽግና ፓርቲ በአሳታፊነት፣ በመረጃ ነጻነት፣ በመሠረተ ልማት እና በስንዴ ልማት ጥሩ ውጤቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል። በሕዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲ ሥራ እና ወደብ እንዲኖር የተጀመረው ሥራም አበረታች መኾኑን ጠቅሰዋል። ሰላም በማስከበር በኩል ለጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት እና ከሕዝቡ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ በኩል የሚቀር ሥራ ስለኾነ በቀጣይ መሠራት አለበትም ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና ተጋባዥ ተሳታፊ አብዱልቃድር እንድሪስ ብልጽግና ፓርቲ እየሠራ ላለው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ በባሕር ዳር ዙሪያ ያለውን የጸጥታ ችግርም በመግባባት እና በመመካከር እንዲፈታ አሳስበዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ሀገሬ ወንዴ የሕዳሴው ግድብ ሥራ እና የሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ ተጠናክረው መቀጠል መልካም እንደኾነ ጠቅሰው ግጭቶች በሰላም እና በእርቅ ተቋጭተው ሰላም እንዲሰፍን ጠይቀዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራም የሰላም ችግርን እንደሚፈታ ነው የተናገሩት።
በኮንፈረንሱ የአማራ ክልል የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተጋባዥነት ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Bitootessa 15/2016