
ጎንደር: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው። በኮንፈረንሱ የተገኙት የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ፓርቲው እንደ ሀገር እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ውጤታማ ተግባራትን እየሠራ ስለመኾኑ አብራርተዋል፡፡ በዚህም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።
ኮንፈረንሱ በሁለት ዓመት ተኩል የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሞ በቀጣይ መሠራት የሚገባቸውን ተግባራት ለመለየት ያለመ መኾኑን ተናግረዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው የሰላም እና ፀጥታ ችግር መኖሩ እንከን መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ባቀረበው የሰላም ጥሪ ከ1 ሺህ 500 በላይ ጥሪውን ለተቀበሉ ወገኖች ሥልጠና በመስጠት ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አንስተዋል። የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ፓርቲው በዞኑ የበጋ መስኖ ልማትን እንደ አዲስ ማስጀመር መቻሉን ተናግረዋል። ለአብነትም በተያዘው ዓመት ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ መልማት መቻሉን አንስተዋል። “ከ90 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል” ብለዋል።
በዞኑ ከ12 ሺህ በላይ ምሩቃን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች መኖራቸውን የገለጹት ኀላፊው በቀሪ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ እነዚህን እና ሌሎች ችግሮችን በመለየት እንደሚቀርፏቸው ነው ያስገነዘቡት። ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ሃሳባቸውን የሰጡን የፓርቲው አባላት ፓርቲው በፈተና ውስጥ ኾኖ ጥሩ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ቅድሚያ ለሰላም በመስጠትም በማኅበረሰቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት መሥራት እንደሚገባም እስረድተዋል።
ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!