
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለሐጅ እና ዑምራ ተጓዦች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለፁ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር የኢፍጣር መርኃ-ግብር ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል።
በመርኃ-ግብሩ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ፤ እንኳን ለታላቁ የረመዳን ወር አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ በዚህ ታላቅ የመሰባሰቢያና የአብሮነት ወር ኢፍጣርን ከእኛ ጋር ለማሳለፍ በመገኘታችሁ የላቀ ምሥጋና ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል።
አየር መንገዱ የደንበኞቹን ምቾት ለመጠበቅ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በየዓመቱ እያሻሻለና እያሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል። ይህንን ተከትሎም ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን የሐጅና ዑምራ ጉዞዎች ለዓመታት ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዘንድሮም ከመላው አፍሪካ የሐጅና ዑምራ ጉዞ ማድረግ የሚፈልጉ ምዕመናንን ለማገልገል አየር መንገዱ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ለሐጅና ዑምራ ተጓዦች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ አየር መንገዱ ላደረገው የኢፍጣር መርኃ-ግብር ምሥጋና አቅርበዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ምክር ቤቱ ከአየር መንገዱ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!