ክልሉ የጀመረውን ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥራ ከተቀመጠለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየሠራ እንደሚገኝ መሬት ቢሮ ገለጸ።

42

ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዛሬው “የት ደረሰ” ዘገባችን በአማራ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥራ ያለበትን ደረጃ እና መቼ እንደሚጠናቀቅ እንዳስሳለን። በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሥራው ተጀምሮ መጠናቀቁን ቀደም ሲልም በተለያዩ ዘገባዎቻችን ጠቁመናል። ዘመናዊ የመሬት አያያዝ ሥርዓት በተሠራባቸው አካባቢዎች ከመሬት የሚገኘው ምጣኔ ሃብት እያደገ መምጣቱን ቢሮው ገልጻል።

ይህ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ በሁሉም አካባቢዎች በወቅቱ መጠናቀቅ እንዳለበት ይታመናል። በመኾኑም አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ሥራው ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ሙሉ በሙሉ መቸ እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ከቢሮው ጋር ቆይታ አድርጓል። የክልሉ መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉትም ሥራውን ከተያዘለት የእቅድ ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ካዳስተር የመሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓት ሲኾን በዋናነት የካርታ እና ገላጭ መረጃዎችን ያካተተ ነው። በኢትዮጵያ ከሚገኘው ከ50 ሚሊዮን በላይ ቁርጥራጭ መሬቶች ውስጥ 28 ሚሊዮኑ የመሬት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንደተሰጠ መረጃዎች ያሳያሉ።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮም በአዋጅ ቁጥር 280/2014 ዓ.ም በተሰጠው ሥልጣን እና ተግባር መሰረት የገጠር መሬት አሥተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን እና በመሬት ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የ10 ዓመት አቅድ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝ የቢሮው ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ገልጸዋል።

ኀላፊው እንዳሉት በክልሉ ከሚገኙ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የመሬት ባለይይዞታ አርሶ አደሮች ውስጥ እስካሁን በ127 ወረዳዎች ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ባለይዞታዎች የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በክልሉ ካለው ከ18 ሚሊዮን በላይ የተበጣጠሰ ማሳ ውስጥ 11 ነጥብ 9 ሚሊዮን ማሳ በካዳስተር ተመዝግቧል።

ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓትም ምዝገባ በመፈጠሩ ከ203 ሺህ በላይ ማሳዎች ለብድር ማስያዣ አገልግሎት እንዲውሉ የማድረግ ሥራ መከናወኑን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ በአርሶ አደሮች መካከል የነበረውን ግጭት ቀንሷል። የአርሶ አደሮች የገቢ አቅም ማደጉንም አንስተዋል።

በክልሉ የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በ10 ዓመት እቅድ ለማጠናቀቅ ቢቀመጥም አሁን በተያዘው ፍጥነት ማከናወን ከተቻለ በሁለት ዓመታት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተገልጿል። ኀላፊው እንዳሉት የገጠር መሬት ምዝገባ ውጤታማ ቢኾንም የከተማን መሬት የይዞታ መብት የማረጋገጥ ሥራ በተገቢው መንገድ እየተሠራ አለመኾኑን ገልጸዋል። በከተሞች ያለው የመሬት አያያዝ፣ አሥተዳደር፣ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ችግሮችን ለመፍታትም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ : መጋቢት 15/2016 ዓ.ስ
Next articleሜጋቢት 15 ም.አ ቺርቤዋ ጋዚቲ