
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደራል መንግሥት የሱፐርቪዥን ቡድን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የክልሉን የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።
ቡድኑ የድጋፍ እና ክትትል ሥራውን አጠናቅቆ የሥራዎችን ጥንካሬ እና ውስንነት ለመገምገም እንዲሁም የፌደራል ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ለመለየት የሚያስችል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል። በዚህ መድረክ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከቡድኑ ጋር ተገናኝተው ምክክር ተደርጓል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እንዳሉት የሱፐርቪዥን ሥራው በሁሉም ክልሎች የሚካሄድ መሆኑን አመላክተዋል። እንደ ሀገር በጋራ ቁሞ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ትልቅ አቅም የሚኾን ነው። ድጋፍ እና ክትትሉ በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎችን ያካተተ እንደነበርም ገልጸዋል። አቶ ይርጋ “እንደሀገር በጋራ አቅዶ እና ተቀናጅቶ የመሥራት፤ ችግሮችንም ተደጋግፎ የመፍታት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል። ወደ አማራ ክልል በመምጣት ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርጉ ከቆዩት የፌደራል መንግሥት የሱፐርቪዥን ቡድን ዓባላት ግብዓት እና ልምድ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መኾኑን በመገንዘብ ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር በፍጥነት እና ሙሉ በሙሉ ለመፍታት እንዲሁም የሕዝቡን ያለስጋት ተዘዋውሮ የማልማት ነጻነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የጋራ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ነው ያሉት። ሕግን ከማስከበር ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችንም አጠናክሮ ለመሥራት የሚያስችሉ ውይይቶች ስለመደረጋቸውም አንስተዋል።
አቶ ይርጋ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የልማት ሥራዎች በፌደራል መንግሥት ጭምር በትኩረት ተይዘው እንዲጠናቀቁ፤ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም እንዲከናወኑ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ ተጀምሯል፤ ከክልሎች ጋር በጋራ በመኾን ወንድም እና እህት የኾነውን ሕዝብም በማቀናጀት ተፈናቃዮችን በሚያረካ መልኩ ለመፈጸም የጋራ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል። የጋራ የኾነች እና የታፈረች ሀገር ለመገንባት ጥሩ የመተጋገዝ፣ የመቀናጀት እና የመናበብ ጅምሮች አሉ፣ በቀጣይ ደግሞ የላቀ ትብብር በመዘርጋት ሀገራዊ ችግሮችን ጨርሶ መፍታት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አማራ ክልል ላይ ሰላም እና ልማት እንደሌለ ተደርጎ ከርቀት ይወራል፤ ቀርቦ ለተመለከተ ግን ብዙ መልካም ነገሮች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ነው ብለዋል። ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ይታመናል፤ እነዚህንም ቢኾን ተጋግዘን እና ተባብረን በመሥራት እየፈታናቸው ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አቶ ይርጋ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ተዋቅሮ ወደ አማራ ክልል የመጣው የሱፐርቪዥን ቡድን በክልሉ ያለውን ችግር ተረድቷል፤ የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ያበጃል ብለዋል። እንደ ሀገር እንዲህ አይነቱ አቅዶ በጋራ የመሥራት እና ተደጋግፎ ችግሮችን የመፍታት ልምድ መልካም መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የፌደራል የሱፐርቪዥን ቡድኑን ድጋፍ እንደ ግብዓት በመጠቀም በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ መሪዎች የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ሥራዎችን በትኩረት በመሥራት ሕዝብን ለማገልገል ቁርጠኞች መኾን እንዳለባቸው አቶ ይርጋ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!