
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት እና መቋቋም የሚያስችሉ የማሻሻያ እና የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ተቋም በማቋቋም በደኖች ላይ ሊደርሱ ለሚችሉ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የሥራ አመራር አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ጌቱ ንጉሴ ከ56 ዓመታት በላይ የተሻገረው ተቋሙ ለሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።
አሁን ላይ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተቋማዊ የማሻሻያ እና የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ መነሻነትም የአሠራር ሥርዓት የሚመራበት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር የፖሊሲ ማሻሻያ ተዘጋጅቶ በ27ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መጽደቁን አስታውሰዋል።
በፖሊሲው በሀገር አቀፍ ደረጃ በአደጋ ሥራ አመራር ላይ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ሊከሰቱ የሚችሉ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት እንደሚቻል አንስተዋል። አደጋን መከላከል፣ መቆጣጠር፣ የከፋ ጉዳት እንዳይደረስ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።
የተናበበ መዋቅር መዘርጋት፣ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲክስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሕዝብ ቁጥር እድገት እና የተቋማት ትብብርን ማሳደግ የፓሊሲ ክለሳው መነሻ ሃሳቦች መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
ከቀበሌ እስከ ፌደራል ተዋረዳዊ የአደጋ ወሰን ብይን በማስቀመጥ በምላሽ አሰጣጥ ሂደት ወቅት ሁሉም መዋቅር የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የሚያደርግ ስለመኾኑም አስንተዋል።
ቅድመ አደጋ ቅነሳ፣ ምላሽ መስጠት፣ አቅም መፍጠር፣ በሰብዓዊ አቅርቦት ማድረግ እና መልሶ ማቋቋም፣ ድህረ አደጋ ልማት እና በቂ ሀብት ማሰባሰብ ዋነኛ የፖሊሲው ዓላማዎች እንደኾኑም አስረድተዋል።
በፖሊሲው የተመላከቱ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት መምራት የሚችል የሰው ሀይል በማዋቀር በጥናት ላይ የተመሰረተ አዲስ ተቋማዊ የማሻሻያ አደረጃጀት መዘርጋት እንደተቻለ ገልጸዋል።
በክልል ደረጃ የሚገኙ የአደረጃጀት ትስስሮችን በማጠናከር ሁሉም መዋቅር እና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንደሚደረግም አንስተዋል።
በፖሊሲው መነሻነትም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ተጠሪ የሆኑ እና ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ተቋት እንደሚቋቋሙ አስታውቀዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት በማቋቋም በተለይም በደኖች ላይ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘውን የእሳት አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በደኖቿ ላይ የሚከሰት የእሳት አደጋን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሂሊኮፕተር ትዋስ ነበር ያሉት አቶ ጌቱ፤ ይህን ለማስቀረትም የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተቋም እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል። አገልግሎቱ ሂሊኮፕተሮች እና ጀልባዎች እንዲኖሩት በማድረግም የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።
በአኹኑ ወቅትም ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በማጠናቀቅ ከተባባሪ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል የሥራ ስምምነት በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሰላምን በማጽናት፣ ልማትን በማፋጠን እና አደጋን ምላሽ በመስጠት በ2013 “ለአደጋ የማይበገር ማኅበረሰብ መፍጠር” የሚል ራዕይ አንግቦ እየሠራ መኾኑን ኢዜአ አስነብቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!