የሸዋሮቢት ከተማን እና አጎራባች አካባቢዎችን የሰላም ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ።

26

ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ኮማንድ ፖስት፣ የቀወት ወረዳ እና የሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር ጠቅላላ የሥራ ኀላፊዎችን ያሳተፈ ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱ በቀጣናው የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሕዝቡ እና የሥራ መሪዎች ጥምረት የተመለከተ እና ችግሩን ለመፍታት መወሰድ በሚገባው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።

የሥራ ኀላፊዎች እስከ ቀበሌ በመግባት የሕዝብ ንቅናቄ መፍጠር እንዳለባቸው ተገልጿል። በተጨማሪም የግንዛቤ ሥራ በመሥራት በማንኛውም የሥራ ዘርፍ ከወረቀት የውሸት ሪፖርት በዘለለ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እና ማስመዝገብ መቻል እንዳለበት ተነስቷል ።

በቀጣይም ቀበሌ በመግባት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት የሚካሄድ ይሆናል። ሕዝቡ የሚያነሳቸው የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ይደመጣሉ ተብሏል። የሥራ ኀላፊዎች የሚነሱ ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመፍታት የሚሠሩበት እንዲሁም እንደ መንግሥት መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች እርምት የሚወስድበት መድረክ እንደሆነ ተገልጿል።

በእለቱ ከሰላም ማስፈን ሥራ በተጨማሪ የገቢ ሥራ፣ የጤና መድኀን፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና የትምህርት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተከናውኗል። መረጃው የቀወት ወረዳ ኮሙኒኬሽን ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ላይ መሥራት እንደሚገባ ተመላከተ።
Next articleየተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ተባለ።