
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ የተመራው የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን በአማራ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን ልዩ የሥራ ድጋፍ እና ክትትል አጠናቅቋል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የልማት እና መልካም አሥተዳደር እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት መቆየቱ ይታወሳል። በክልሉ ቆይታው የተመለከታቸውን ጠንካራ ሥራዎች እና መታረም ያለባቸውን ውስንነቶች ለይቶ ለክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ግብረ መልስ ሰጥቷል።
ግብረ መልሱን በማደራጀት ለክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ያቀረቡት ጫልቱ ሳኒ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተፈትቶ ሰላም እንዲሰፍን ጠንካራ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን አመላክተዋል። ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ጠንካራ የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች እየተከናወኑ ነውም ብለዋል።
ሚኒስትሯ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን መመልከታቸውንም አረጋግጠዋል። በዚህ ዘርፍ በተለይም ባሕር ዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ላይ የተሠሩ ሥራዎች ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ናቸው ብለዋል።
ክልሉ በጸጥታ ችግር ውስጥ ቢኾንም አቅም እና አመለካከታቸው የዳበረ፣ ለሕዝብ በቁርጠኝነት የሚሠሩ አዳዲስ መሪዎችን ማደራጀት ተችሏል ብለዋል ሚኒስትሯ። በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮችን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ ወደ ውስጥ በመመልከት፣ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ማጽናት እና ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት በመግባት ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ሲሉም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተለይም “እጅ መንሻ የመጠየቅ” ብልሹ አሠራር እንዳለ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። ይህ አካሄድ በፍጥነት ተቀርፎ ለዜጎች የተቀላጠፈ እና ፍትሐዊ የኾነ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) የሱፐርቪዥኑ ዋና ዓላማ በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት በጋራ የታቀዱ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ሥራዎች ያሉበትን ኹኔታ ለመመልከት ነው ብለዋል። ጥንካሬ እና ውስንነቶችን በመለየት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሥራዎች በቅርበት ለመደገፍ ያለመ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ምልከታው የክልሉን ሕዝብ የልማት ጥያቄ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል ዶክተር ለገሰ። ክልሉ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት መኾኑን በምልከታ አረጋግጠናል ያሉት ሚኒስትሩ አሁንም ድረስ ጽንፈኛ ኃይል እንቅስቃሴ የሚያደርግባቸው ኪስ አካባቢዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል። ይህ ችግር በቅርብ ቀን መፍትሔ አግኝቶ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሰላማቸው እንዲረጋገጥ፣ ሕዝቡ እፎይታን አግኝቶ በሙሉ ልቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ እና ትምህርታቸው የተቋረጠባቸው ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የክልሉ የግብርና ሥራ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ሚኒስትሩ የማዳበሪያ እና ሌሎች ግብዓቶች ስርጭት ወደየአካባቢዎቹ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል። የፌዴራል መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በያዘው ቁርጠኝነት መሰረት የማዳበሪያ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶት እየቀረበ ነው፤ ግብዓትም በተለይም የስንዴ እና በቆሎ ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው ብለዋል።
በሰሜን ጎንደር እና አካባቢው ሰፊ ምልከታ እንዳደረጉ የገለጹት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲወስ (ዶ.ር) የአካባቢውን የጸጥታ ተቋማት ከማጠናከር አኳያ አበረታች ሥራ ተከናውኗል፣ አካባቢውም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ነው ብለዋል። ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል። ምልከታ ባደረጉባቸው አካባቢዎች ሕዝብ የሚያነሳቸውን ውስንነቶች ለየአካባቢዎች መሪዎች ግብረ መልስ የሰጡ ሲኾን በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንዲያገኙም ይሠራል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀንዓ ያደታ (ዶ.ር) የጸጥታ ተቋማትን በማጥራት እና መልሶ በማደራጀት በኩል እንዲሁም ክልሉን ከገጠመው የጸጥታ ችግር በማውጣት በኩል ጠንካራ ሥራ መከናወኑን ተመልክተናል ብለዋል። በክልሉ የከፋ የጸጥታ ችግር እንዳለ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ትክክል አለመኾኑን በአካል ተገኝተው ማረጋገጥ ስለመቻላቸውም ገልጸዋል። በመንግሥት እና በግለሰብ ባለሃብቶች በመገንባት ላይ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችም በጠንካራ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸው አበረታች መኾኑንም ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ድጋፍን የሚፈልጉ ሥራዎች እንዳሉም ዶክተር ቀንዓ ተናግረዋል። በተለይም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በትኩረት ተይዘው መጠናቀቅ እንዳለባቸው ተገንዝበናል ነው ያሉት። እንደ መብራት፣ መንገድ እና ቴሌኮም የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት በኩል የፌዴራሉ መንግሥት በትኩረት መሥራት እንዳለበትም ተመልክተናል፤ ይህንንም ለሚመለከተው አካል ሁሉ አድርሰን መፍትሔ ለመስጠት በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ.ር) በክልሉ የነበረው ድጋፍ እና ክትትል የግብርና ሥራውን ለመደገፍ የሚያስችል ነው ብለዋል። የመኸር እርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አበረታች ነው፤ ለክረምት እርሻ የሚያገለግሉ ግብዓቶች አቅርቦት እና ሥርጭት እየተከናወነ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የግብርና ሥራ ፍጹም ሰላምን ይፈልጋል፤ ማኅበረሰቡ የየአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ልማቱን ማከናወን እና የሁሉም ነገር መሰረት የኾነውን ኢኮኖሚ መደገፍ አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!