
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሀገሪቱ ያለውን የታዳሽ ኃይል አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመጨመር ዕቅድ መያዙን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በርካታ የነዳጅ መኪኖች ወደ ሀገር እንዳይገቡ መከልከላቸውም ተመላክቷል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሐሰን የሀገሪቱን የታዳሽ ኀይል አቅም መጠቀም የሚችል የትራንስፖርት ዘርፉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመጨመር ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
እንደ አቶ በርኦ ገለጻ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው የቀረጥ ማበረታቻ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እየገቡ ነው። በአሁኑ ጊዜም ከውጭ የገቡ እና በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ያደረገው የቀረጥ ማበረታቻ የባለሀብቱ ተነሳሽነት እና የሀገሪቷን የታዳሽ ኀይል አቅርቦት ለማሳደግ እንዲሁም የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ያለው የታዳሽ ኃይል አቅም ሰፊ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ያለውን የታዳሽ ኀይል በአግባቡ የሚጠቀም፣ በማኅበረሰቡ ጤና እና በአካባቢ ብክለት ላይ ጉዳት የማያስከትል አረንጓዴ ትራንስፖርት በ10 ዓመቱ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በ10 ዓመት ውስጥ 439 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ሁለት ሺህ 335 የኀይል መሙያ ማዕከል እንደሚኖሩ አብራርተዋል። ይህን ዕቅድ ለማሳካት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ሀገሪቱ በዓመት የምታወጣውን አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ወጪ ለመቀነስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም እና ከውጭ ሀገራት በስፋት ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በርካታ የነዳጅ መኪኖች ከውጭ እንዳይገቡ እንደተከለከሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። ከባድ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች ማለትም ለግብርና ግብዓት፣ ለውኃ ቁፋሮ እና ለሌሎች መሰል አገልግሎቶች የሚውሉ መኪኖች አለመከልከላቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ተቀይረው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የተሽከርካሪ አይነቶችን በመለየት ወደ ሀገር እንዲገቡ ይደረጋል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ዘርፉን ከነዳጅ ጥገኝነት በማላቀቅ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። ኢፕድ እንደዘገበው ዘርፉ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ በመኾኑ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለግል ዘርፉ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ እና ከአየር ብክለት መከላከል ባለፈ የድምፅ ብክለትን ለማስቀረት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን የሚረዱ መኾናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድሩት የኢኮኖሚ ጫና በተጨማሪም ለሕገወጥ ገበያ፣ ለአየር እና ለድምፅ ብክለት ምክንያት መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!