
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለዛሬ የትዝብት አምድ መነሻ የኾነኝ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያስተዋልኳቸው ጉዳዮች ናቸው ።
ቀለል ያለ ህክምና ለማግኘት ጎራ ያልኩበት አንድ የጤና ተቋም የታዘብኩትን በማስቀደም ልጀምር። በሥራ ምክንያት ህክምና ለማግኘት ጠዋት ስላልተመቸኝ ጎራ ያልኩት ከቀኑ በ7:30 ሰዓት ነበር። በዚህ ወቅት ታካሚ እና አስታማሚ ካርድ ክፍል በር አካባቢ ተሠባሥበናል።
ከካርድ ክፍል እስከ ሀኪሞች አብዛኞቹ ሠራተኞች ‘ለምሳ ስለሄዱ’ በቢሯቸው አልነበሩም። በሽተኛ እና አስታማሚ በየበረንዳው እና በየወንበሩ በመጠባበቅ ላይ ነን። ታካሚዎቹ እንደነገሩኝ የአንዳንዶቹ ካርድ ክፍል ላይ፣ የአንዳንዶቹ የደምና የሽንት ምርመራ ላይ፣ የቀሪዎቹ ደግሞ መድኃኒት ክፍል ላይ እንደደረሰ ነው በምሳ ሰዓት ምክንያት የህክምና ሂደቱ የተቋረጠባቸውና ለከሰዓት የተቀጠሩት። ህክምናቸው አልቆላቸው የሄዱም እንዳሉ ሰምቻለሁ።
የጥበቃ ሠራተኛው ዱላውን ይዞ በየሥራ ክፍሎቹ እየተንቀሳቀሰ ይቃኛል። ቢጨንቀን ”በምሳ ሰዓት ህክምና የለም እንዴ” ስንል ጠየቅነው።
”ሲመስላቸው ያክማሉ፤ ሲፈልጉ ደግሞ ዘጋግተውት ይሄዳሉ” በማለት ያስተዋለውን እና የተሰማውን በቅንነት ነገረን።
ዛሬ በህክምናው ዓለም በተለይም በመንግሥት የጤና ተቋማት የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ከካርድ ክፍል እስከ መድኃኒት እና ቀዶ ህክምናው ድረስ ”ሰው የሌለው” ሰው ተገቢ ህክምና ማግኘት እንደማይቻል ኅብረተሰቡ የተስማማበት ሀቅ እየኾነ መጥቷል።
ለሥራ ቅጥር ከሚደረግ የጤና ምርመራ ደም እየፈሰሰው እስከመጣ ታካሚ ድረስ የምሳ ሰዓት አልፎ የቢሮ መግቢያ እስኪደርስ ድረስ ጠበቅን። ”ሀኪሞቹ” በሰባት ሰዓት ተኩል ሥራ ከመጀመር ይልቅ ካንዱ ክፍል አንዱ ክፍል ሲሉ ቆዩ። ስምንት ሰዓት ሲኾን ካርድ ክፍል ተከፈተ፣ ባለሙያዎችም ወደየሥራ ክፍላቸው ገቡ።
እንዲያም ኾኖ ሥራ አልጀመሩም። ሁለት የክፍሉ ሠራተኞች ምን እንደሚፈልጉ እንጃ ከመደርደሪያ ጠረጴዛ፣ ከመሳቢያ ፖርሳ ሳይቀር በፍለጋ ይደክማሉ። ታካሚዎች ደግሞ በጠራራ ፀሐይ ተሰልፈን እንጠባበቃለን። ተቆጥተው እንዳይዘጉብን በፍርሃት እና በስጋት ተሸብበን ቆየን። ከመካከላችን አንዱ ደፋር ”ወንድሜ ሥራ ጀምሩ እንጂ!” ሲል በተማረረ ስሜት ተናገረ።
”ታገሱን እንጂ እየሠራንኮ ነው” አንዱ ካርድ ክፍል የታካሚ ካርድ እያገላበጠ ፊቱን አኮሳትሮ መለሰ።
” ገና ጧት የመጣን ካርድ እንኳ ማውጣት ሳንችል መሸ እኮ”
”እሱ አይመለከተኝም”
”ይመለከትሃል እንጂ! ካርድ መስጠት ያለበት ማን ነው?” ሲል ክርክሩን ቀጠለ።
”መስተካከል ያለበት ነገር ስላለ ነው ታገስ ወንድም” ወደ ቁጣና ተግሳጽ ያደላ መልስ ነበር።
”ታገስኩኮ። ገና ጧት የመጣሁ ስምንት ሰዓትም ካርድ ላገኝ አልቻልኩም፤ እስከ መቼ ነው የምትታገሰው?”
ለካርድ የተሰለፈው ሌላው ሰው ”በቃ ተውት” በማለት በገዛ ጉዳዩ ገላጋይ ኾነ።
በዚህ መካከል ነጭ ጋወን የለበሰ ባለሙያ (ሀኪም መሰለኝ) ካርድ ክፍል ገባ። የሚሠራውን መከታተል ያዝን። የካርድ ክፍል ሠራተኞቹን ዝቅ ባለ ድምጽ ጥቂት አወራና ትዕዛዝ አዘዘ፤ እሺ አሉት። ከክፍሉ ሲወጣም ለካርድ የተሰለፈውን ሰው በአይኑ ገረመመ። ያ ቀድሞ የጠየቀ ሰው ”ኧረ ወንድም ተመካከሩና አስተናግዱን” ሲል ጠየቀ።
ሀኪሙም ”ታገሱ እንጂ እየሠራንኮ ነው” አለ
”ይኼው ቆመንኮ እየተጉላላን ነው፤ ማስተናገድም አልጀመራችሁም፤ ወይ ችግር ካለ ንገሩን”
”በቤትህ ወይ በመሥሪያ ቤትህ ችግር ገጥሞህ አያውቅም?”
”ችግርማ ምን ጠፍቶ፤ እኛ ያልነው ወይ ሥራ ጀምሩ ወይ ችግሩን ንገሩን ነው”
”እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?” በማለት ችግሩንም ሳይፈታ ከካርድ ክፍል ወጣ።
”ምንም ማድረግ ካልቻልክ መፍትሄ እንደሚሰጥ ሰው ለምን ታለፋኛለህ?”
ሀኪሙ የተሠበሠበውን ሰው በንቀት ገላምጦ ወደ ክፍሉ ሄደ።
በእንዲህ ያለ ሁኔታ ብዙ ጊዜ አለፈ። ካርድ ክፍሎችም ለሥራ ያስቸገራቸው ነገር ሚስጥር እንደኾነ ቆየ። ቀለል ላለ ህክምና የሄድነው ተስፋ ቆርጠን ከጤና ጣቢያው ስንወጣ የባሰ ችግር ያለባቸው ከዚያው ቀሩ።
በየመሥሪያ ቤቱ የተቀጠሩ እንዲህ ያሉ ስመ ”አገልጋዮች” በርካታ መኾናቸው ይሰማኛል። ግልጽነት የለ፣ ሲጠየቁ ትክክል እና እውነተኛውን መናገር የለ፣ ይባስ ብሎ መብቱን የጠየቀ ተገልጋይን የተለየና አስቸጋሪ አድርጎ በመፈረጅ ለማሸማቀቅ እና ለመነጠል መሞከር የበርካታ ልግመኛ ሠራተኞች ባህሪ ኾኖ አስተውያለሁ።
የሚገርመው እንደነዚህ ያሉ ሠራተኞች ናቸው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የራሳቸውን ግዴታ ሳይወጡ እገሌ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ፤ እንትና ደግሞ ይህንን ሳይሠራ በሚል እጥረት እና ችግሮችን ሁሉ ”ለሌላ አካል” ሲያሸክሙ የሚታዩት።
ዛሬ ዛሬ አንድ መሥሪያ ቤት የሄደ ሰው በፍጥነት ለመገልገል ባለሥልጣን፣ ባለወገን ወይ ባለሃብት መኾን ቅድመ ሁኔታ መስሏል። ካልኾነ ግን መጉላላት ወይ ተስፋ ቆርጦ መመለስ እጣ ፈንታው ይኾናል። እድለኛ ኾኖ ቅንና አገልጋይ ሠራተኛ አጋጥሞት በአግባቡ ከተስተናገደ ሎተሪ እንደወጣለት ጮቤ እየረገጠ እና እያመሠገነ ይመለሳል።
የሀገራችን ”ሲቪል ሠርቪስ” ችግሩ ገና የመሥሪያ ቤቱ የአጥር በር ሲደርሱ ማነህ፣ ወዴት ነህ በሚል ፖሊያዊ ምርመራ ችግር ላይፈቱ ናላን ካዞሩ በኋላ ‘እስኪ ግባና ጠይቅ’ ከሚሉ የጥበቃ ሠራተኞች ይጀምራል። የሥራ ክፍሉን አግኝተው ሲገቡ በክብር እንዲቀመጡ ከመጋበዝ ይልቅ በውክቢያ ማንን እንደሚፈልጉ ይጠየቃሉ።
ከኀላፊው ጉዳይ እንዳለዎት ቢናገሩም ለምንኛው ጉዳይ እንደኾነ ማብራራት ይጠበቅብዎታል። ጸሐፊዋ ችግር እንደሚፈታ ሰው ሌሎች ጓደኞቿ ባሉበት ጭምር ሚስጥርዎን ታስዘረዝርዎታለች። በጥያቄ ካናዘዘችዎ በኋላ ኀላፊው አለመኖራቸውን ገልጻ ”ምናልባት እዛኛው የሥራ ክፍል ይጠይቁ” በማለት ታሰናብትዎታለች።
የቀጣዩ የሥራ ክፍል ጸሐፊም ተቀብላ እንደገና ታናዝዘዎታለች። ኀላፊዎቹ የት ይገኛሉ – አያውቁም፤ ጉዳዩን ማን ይፈጽምልኝ – ‘አላወኩም’ ምላሻቸው ነው፤ ‘ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ደግሞ ማስተዛዘኛ ቃላት ይሰነዘርልዎታል።
ትዝብቴን ቀጥያለሁ እናንተም እየተከተላችሁኝ እንደኾነ ተስፋ አደር ጋለው እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ሌላ ተቋም ጎራ እንበል። የዛሬ ዓመት አካባቢ አንዲት በቅርብ ኀላፊዋ ወንጀል የተፈጸመባት ሠራተኛ በደሏን ወደ ፍርድ ቤት ወስዳ አስፈረደች። በፍርዱ መሠረት የምታገኘውን መብት በውክልና ለማስፈጸም ስለሰጠችኝ ወደ አንድ የዞን መሥሪያ ቤት ጎራ ብያለው።
የተቀበለችኝ ጸሐፊ ከሁለት ጓደኞቿ ጋር ኾና እና አንገቷን ኮምፒዩተሯ ላይ ደፍታ ጉዳዩን መረመረች። የሥራ ባልደረቦቿ እየሰሙ ካናዘዘችኝ በኋላ ይህን ጉዳይ የሚመለከተው አንቺን ነው ብላ ከአጠገቧ ላለች ባልደረባዋ ከነጉዳዩ መራችኝ። ተረኛዋ በፈንታዋ መረመረችኝና ለሥራ ኀላፊዋ መራችኝ፤ የሥራ ኀላፊዋ ለፍትሕ- ፍትሕ መልሶ ለሌላ ተቋም እንዲህ እያለ በደል የደረሰባትን መምህር ጥያቄ አስተናግዶ ለመፍታት ትምህርት፣ ሴቶች እና የፍትሕ ተቋማት ያውም ሴት ባለሙያ እና ኀላፊዎች ጉዳዩን ሲገባበዙት እና ሲገፋፉት እንደማየት ምን አሳዛኝ ነገር አለ!
በታዘብኳቸው የውይይት መድረኮች እና የተናጠል ጭውውቶች ሁሉ ከባቢያዊ እና ሀገራዊ ችግሮችን አርሶ አደሩ ወይም ድሃው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰጠውን ትምህርት ያለመቀበል እና ያለመተግበር እንደኾነ የሚበይኑ በርካቶች ናቸው ይህም ችግሮችን ለሌላ አካል ማሸከም እንደማለት ነው። ሀገር በድህነት የምትማቅቀው ‘አርሶ አደሩ የተሻሻሉ አሠራሮችን አለመቀበሉ፣ ማኅበራዊ እና የምጣኔ ሃብት መስተጋብሩን አለማዘመኑ ነው’ በሚል ፍርደ ገምድል ብያኔ የሚሰጠው የመንግሥት ሠራተኛ እና ምሁር ከድክመቶቹ ሲማር አይስተዋልም።
አርሶ አደሩን ‘ምክር የማይሰማ’ እና ‘ተረጂ’ በማለት የሚፈርጁ ሰዎች ከእርዳታ እና ብድር የተገኘን በጀት በደመወዝ እና አበል መልኩ እያገኙ መኾኑንም ይዘነጋሉ። አበል ለማግኘት በማይመለከታቸው ጉዳይ ሥብሠባ ካልተሳተፍኩ በሚል ”ለገላጋይ የሚያስቸግሩት” እና ሦስት ቀን ተሠብሥበው የአምስት ቀን አበል የሚወስዱ ምሁራን ለሀገሪቱ ችግር ተጠያቂ አርሶ አደሩን ሲያደርጉ መስማት ተለምዷል።
ለአርሶ አደሩ በሚሰጥ የእርዳታ እህል ምክንያት ከሚረክስ ገበያ እየገዛና ”ለኑሮ መደጎሚያ” እየተጠቀመ ድህነትን ለመቀነስ ትልቁን ኀላፊነት በአርሶ አደሩ ላይ ብቻ ማላከክ የብዙዎቻችን የአመለካከት እና ችግሮችን ወደ ውስጥ ያለማየት ክፍተት ኾኖ ይታየኛል። በግብርናው፣ በጤናው፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት፣… ብቻ አርሶ አደሩን በማስተማር፣ በማሠልጠን እና በመቀየር ለተሻለ ሕይወት በማብቃት የተሻለች ሀገር የመፍጠርን የየመሥሪያ ቤታችን ራዕይ እና ተልዕኮዎች ረስተን የመፍትሄ ኀላፊነቱን ለአርሶ አደሩ የምናሸክም በርካቶች ነን።
በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ እና በየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ አብዛኛው ማኅበረሰብ የሚስማማበት ጉዳይ ቢኖር ችግር መኖሩን ብቻ ነው። በችግሮቹ መነሻ እና በመፍትሄዎቻቸው ላይ ግን ተጠያቂነትንም በመውሰድ በኩል የማኅበረሰብ ስብራት ይስተዋላል።
በሸንጎ እና በሥብሠባ አዳራሾች ስለ ፍትሕ መጓደል፣ ስለ አገልግጋይነት ስሜት መዳከም፣ ስለ ሙስና እና መሰል እውነቱን ከሕግ፣ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት እና ከሞራል ፍልስፍና አኳያ እያነጻጸረ ‘የሥርዓቱ ሰዎችን’ ወይም ‘ሥርዓቱን’ ሲወቅስ የዋለ ሰው ጨለማን ተገን አድርጎ ባለስልጣናትን እና ጉዳይ ፈጻሚዎችን በየሆቴሉ ሲጋብዝ እና ”የኔን ነገር እንዴት ነው” በሚል በእጅ መንሻ ልምምጥና ምልጃ ላይ ታገኙታላችሁ። በቃ! እኛ እንደማኅበረሰብ እንዲህ እየወረድን ነው።
በችግሮቻችን ላይ ሰክኖ በመወያየት ምንጫቸውን ከነመፍትሄዎቻቸው መርምሮ ወደ ራስ ከማማተር ይልቅ የችግሩን ምንጭ ”በሌሎች” የማሳበብ እና መፍትሄውንም ”ከሌሎች” የመጠበቅ አባዜ በምንተነፍሰው አየር እና በምንጠጣው ውኃ ወደ ውስጣችን ገብቶ የተዋሃደን ይመስላል።
አሁን አሁን በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በሃይማኖት፣ በባሕል እና በታሪክ ለሚገጥሙን ችግሮች መፍትሄ ‘ምን እናድርግ’ ከማለት ይልቅ ‘ተሠርቶብን’ ማለት እየቀናን ነው። አውሮፓውያን ሠርተውብን ማለቱ ዝቅ ሲልም ”በዚያኛው” ብሔር ወይም ሃይማኖት ተከታይ ላይ ማላከክ አብሮን የተፈጠረ መስሏል።
‘አውቃለሁ’፣ ‘እችላለሁ’ እንላለን። ነገር ግን እውቀታችን እና የነገሮች ትንታኔያችን የችግሮቻችን ምንጭ እንኳ በትክክል መለየት አላስችለን ብሎ ትዝብት ውስጥ ይጥለናል፤ አለፍ ሲልም ያስንቀናል። የማኅበረሰብ እና የሀገር ችግሮችን ውጫዊ ለማድረግ ስንታትር እንገኛለን። ተስቶን ይህ የራሳችን ችግር ነው፤ ”’በራሳችን ችግር ውስጥ” የኔም ድርሻ አለበት ብሎ ለማሰብ እና ለመናገር ፍላጎትም ወኔም እናጣለን።
ሥርዓተ መንግሥት ዓለማዊ እንጂ የነፍስ ሥራ እንዳልኾነ ማሰብ ያቅተናል። ችግሮቻችንን ለይተን ራሳችንን ከማረም ይልቅ ለሌሎች እና ለመንግሥት የማሸከም የአስተሳሰብ ዝንፈት ይታይብናል። መንግሥት እና ባለሥልጣናቱ ጻዲቅ እንዲኾኑ የመጠበቅ ገራገርነት የሚታይባቸውም በርካታ ናቸው።
ካለፈው ጊዜ ትምህርት በመውሰድ እና በመወያየት የራሳችን ችግር ራሳችን በቅደም ተከተል ካልፈታን ማን እንዲፈታልን ነው የምንፈልገው? ወይስ እንዳማረርን እና ችግሮችን በሌላ አካል እንዳሳበብን የዓለም ፍጻሜን መጠበቅ ነው የመረጥነው?
ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሕዝብ እና መንግሥት ባላቸው መስተጋብር የሚያጋጥሙንን የሕይወት ጉዞ እንቅፋቶች በቅንነት በመመካከር የየድርሻችን መውሰድ አቅቶናል። ”በዚያኛው አካል” ጫማ ቆመን ከማሰብና ከመፍረድ ይልቅ ጥፋትን እና ተጠያቂነትን ለሌላው አካል የማሸከም ወረርሽኝ ተሰራጭቶብናል። እኔም ኀላፊነት አለብኝ፤ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ለቾግሮች ድረሻ አለኝ ብለን በቅንነት ከማሰብ ይልቅ ‘እኔ ደሞ ምን አድርጌ’ በሚል ስህተትን አለመቀበል ፋሽን ኾኗል። ችግር ብለን እንደየምንበይናቸው የየጊዜው ተግዳሮቶች የበላይ ኀላፊን፣ መንግሥትን ወይም ሌሎች አካላትን ተጠያቂ በማድረግ መውቀስና መርገም ባሕል እየኾነብን ነው።
የብሔር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነቶቻችን ተፈጥሯዊ ሳይኾን ‘የዛኛው አካል ድክመት እና መጥፎነት’ አድርጎ ከመፈረጅ ደዌ መታከም ያስፈልገናል። በልዩነቶቻችን ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ብንችል ”በእኛ አሸናፊነት” ካልኾነም ”በዚያኛው አካል ተጠያቂነት” እንጂ በጋራ ጥቅም እና አሸናፊነት የሚቋጭ የልዩነት አፈታት ባሕል ገና አላዳበርንም።
የማነስና የመብዛት ጉዳይ እንጂ ለእጥረቶች አበርክቶ አለኝ፤ ለመፍትሄውም ኀላፊነት ልወስድ ይገባል። ከግል ወይም ከጠባብ አስተሳሰብ ተጠቃሚነት እና አሸናፊነት ይልቅ የወል፣ ሰፊ እና ሀገራዊ እሴቶችን በመፍጠር እና በማጠናከር አብሮ ዘመናትን ለመሻገር ከአሁኑ ማስተዋል ያስፈልገናል።
የየደረጃው የመንግሥት አካላትም ጥሩ ውጤት እና ስኬት የሚመስሉ ነገሮች ሲገኙ ”መተኪያ በሌለው ፖሊሲ እና ስትራቴጅ፤ በጠንካራ እና ቁርጠኛ መዋቅር እና አመራር” ሲሉ ይስተዋላል ችግሮች ሲገጥሙ ደግሞ ለሌላ ማሻገር የተለመደ ኾኗል።
በመኾኑም በየደረጃው ያሉ መሪዎች እና ባለሙያዎች ከኔ በላይ ላሳር ከማለት ወጥተው ከሁሉም ሕዝብ እና ተቋማት ጋር በቅንነት በመወያየት፣ በመተማመን እና ተግባራዊ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ እንደማኅበረሰብ እያጠቃን ካለው ሁሉን ነገር ውጫዊ የማድረግ በሽታ እንድንፈወስ የመሪነቱን ሚና በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!