
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ዕረፍት። ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር፣ በመንዝ አውራጃ፣ በአንኮበር ወረዳ ደረፎ ማርያም በምትባል ስፍራ ተወለዱ፡፡
ልዑልነታቸው የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የሣኅለሥላሴ ልጅ የልዕልት ተናኜወርቅ ሣኅለሥላሴ እና የደጃዝማች ወልደሚካኤል ወልደመለኮት ልጅ ናቸው። ውልደታቸው ግንቦት 1 ቀን 1844 ዓ.ም ነው፡፡ እስከ 14 ዓመታቸው ድረስ ከአባታቸው ጋር ኖረዋል። በኋላም አጎታቸው ወደኾኑት የንጉሥ ኃይለመለኮት ልጅ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሂደው ባለሟል ኾኑ፡፡
በ1879 ዓ.ም የሐረር ግዛትን እንዲያሥተዳድሩ ተሾሙ፡፡ በዓድዋ ጦርነት የደቡብ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ኾነው ገድል የሠሩት ልዑል ራስ መኮንን የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ምኒልክ ተወካይ ኾነው የአውሮፓ ሀገሮችን ጎብኝተዋል።
ጣሊያንን በጎበኙ ጊዜ የጣሊያን ጋዜጦች የውጫሌ ውልን በተመለከተ “..በውጫሌ ውል ላይ ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥገኝነት ተቀብላ ውል ከፈረመች በኋላ የጀርመን ንጉሠ ነገሥት ከኢትዮጵያ የሚላከውን ማንኛውንም ደብዳቤም ኾነ ጉዳይ በጣሊያን መንግሥት በኩል መቀበል ሲገባቸው በቀጥታ ከምኒልክ የተጻፈውን ደብዳቤ ተቀብለዋል…” እያሉ በመጻፋቸው ራስ መኮንን ይህንኑ ተቃውመው ለጣሊያን መንግሥት ነግረዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰውም የውሉን መበላሸት ለአጼ ምኒልክ አሳውቀዋል፡፡
በተፈጥሯቸው የታደሉት ዲፕሎማሲያዊ ስብዕና ያላቸው እንደነበሩ የሚነገርላቸው ልዑል ራስ መኮንን የተፈሪ መኮንን (የወደፊቱን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) ወላጅ አባትም ናቸው፡፡
በ1888 ዓ.ም ከጣሊያን ጋር በተደረገው ጦርነት ራስ መኮንን 15 ሺህ እግረኛ ወታደሮችን ይዘው ከምኒልክ እና ታላላቅ ጦር አዛዦች ጋር ዘምተዋል። በህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም ከሌሎች የጦር አበጋዞች ጋር ኾነው አምባላጌ ላይ የመሸገውን የጣሊያን ጦር ተፋልመዋል፡፡ በዚህም የጣሊያን ጦር መሪ ሜጆር ቶዞሊ ተገድሎ ምሽጉን አስለቅቀዋል፡፡ ጦርነቱም በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ተጠናቋል፡፡
ጠላትን ተከታትለው መቀሌ ምሽግ አድርሰው በመክበብ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ብልህነት እና የጦር መኮንኖች እና ኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ ተጨምሮበት መቀሌ ምሽግን ማስለቀቅ እና በርካታ መሣሪያ ሲማረክ ልዑል ራስ መኮንን አበርክቷቸው ከፍተኛ ነበር፡፡
በዓድዋው ጦርነት የጄኔራል አልበርቶኒ እና ዳቦር ሜዳ ጦር እንዳይገናኝ ከራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ከወሎው ንጉስ ሚካኤል፣ ከራስ ወሌ ብጡል እና ከዋግሹም ጓንጉል ጋር በመኾን 18 ሺህ ጦር ይዘው ጉሶሶ በተባለው ተራራ ላይ ሠፈሩ፡፡ በዚህም የጣሊያንን ጦር ቆርጠው እና ከብበው በመዋጋት ለዓድዋ ድል አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
እኒህ የኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ያረፉት በዚህ ሳምንት መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ነበር፡፡
ምንጭ:-
• “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” – ቀ.ኃ.ሥ. 1929 ዓ.ም
• “አጤ ምኒልክ” – ጳውሎስ ኞኞ 1984 ዓ.ም
• “የኢትዮጵያ ታሪክ – ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ” ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም
——————-//——————
ለዓለም ፖስታ ማኅበር አባልነት ከኢትዮጵያ የተጻፈ ደብዳቤ
‹‹ምን ይልክ፣ ምን ይልክ፣ ምን ይልክ እያሉ
በፖስታ ቤት ዙርያ ይጠያየቃሉ፡፡
ዛሬማ ምን አይልክ!
ሁሉን በየዓይነቱ ሰፍሮ በልክ በልክ
ብቅ ብሎ ባየው መሥራቹ ምን ይልክ፡፡››
ይህ ግጥም ከ130 ዓመታት በፊት የተጀመረውን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የሚዘክር ነው፡፡
የኢትዮጵያን ግዛት በማስፋት እና ከቅኝ ግዛት በመከላከል ተጠቃሹ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በሥልጣኔ ወዳድነታቸውም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዛሬ 129 ዓመት በፊት የተጀመረው የፖስታ አገልግሎት ከማሳያዎቹ መካከል አንዱ ነው፡፡
ንጉሡ ኢትዮጵያን የዓለም ፖስታ ማኅበር አባል እንድትኾን የሚጠይቅ ደብዳቤ በየካቲት 1885 ዓ.ም የላኩ ቢኾንም የተሰጣቸው ምላሽ በቅድሚያ የፖስታ ሥራ ማካሄዱን እንዲጀምሩ ነበር። በመኾኑም የፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ1886 ዓ.ም በአዋጅ እንዲቋቋም አደረጉ፡፡ በምስላቸው የተቀረጸ ቴምብርም በሥራ ላይ አዋሉ። ይህን ካደረጉ በኋላ ነበር በድጋሚ ለዓለም ፖስታ ድርጅት የአባልነት ጥያቄ ደብዳቤ የጻፉት፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያን የፖስታ አገልግሎት ለማቋቋም እና የዓለም ፖስታ ማኅበር አባል ለመኾን ለስዊዝ ፕሬዚዳንት በድጋሜ ደብዳቤ የላኩት በያዝነው ሳምንት መጋቢት 10 ቀን 1887 ዓ.ም ነበር።
ስለ ኢትዮጵያ የዓለም ፖስታ ማኅበር አባልነት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ተደጋጋሚ የመልዕክት ልውውጦች አድርገዋል፡፡ በአንድ ወቅት የጻፉት ደብዳቤም የሚከተለው ነበር፡፡
“የኢትዮጵያ፡ ቴሌግራፍና፡ ፖስታ፡ እንደ፡ ሮፓ፣ መንግሥት፡ ደንብ፡ ከኡኒዮን፡ ፖስታ እንዲገባ፡ አስታዉቃለሁ፡፡ ሌሎች፡ መንግሥቶች፡ እንደሚከፍሉት፡ ገንዘብ፡ እኛም፡ ባመት እንደ፡ ደንቡ፡ ለኡኒዮን፡ ፖስታል፡ እንሰጣለን፡፡ የፖስታና፡ ቴሌግራፍ፡ ሠራተኞች፡ ከዚህ ቀደም፡ ስድስት ሰዎች፡ እንድታስመጣልን፡ ጠይቀንኽ፡ ነበር፡፡ አሁንም፡ በቶሎ እንድታስመጣልን፡ ይሁን፡፡ ደሞዛቸውንም፡ እንደ ሥራቸው፡ መጠን፡ ከመቶ አንስቶ እስከ፡ መቶ፡ አምሳ፡ ድረስ፡ በተዋረድ፡ እንሰጣለን፡፡…”በማለት እንዳሳሰቡ በታሪክ ተከትቧል፡፡ በ1901 ዓ.ም ኢትዮጵያ የዓለም የፖስታ ኅብረት አባል ኾናለች፡፡
ምንጭ፡-
• ጳውሎስ ኞኞ
• የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ድረ ገጽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!