በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

35

ከሚሴ: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በመገኘት እየተከናወኑ የሚገኙ የግብርና እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶችን ጎብኝተዋል፡፡ ሚኒስትሩ የተመለከቷቸው የመስኖ ልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከገበያ ትስስር ጋር የሚስተዋሉ የአርሶ አደሮችን ችግሮች ለመቅረፍ የፌዴራል እና የክልሉ አመራሮች በጋራ በመኾን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ይሰጣሉ ብለዋል። እንደ ሀገር ይፋ የተደረገውን የአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ቱሩፋት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንደ በአካባቢው የተቀናጀ የግብርና ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰይድ ሀሰን በዞኑ 16 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ አስካሁን 14 ሺህ ሄክታር መሬት እንደለማ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም 10 ሺህ ሄክታር መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ መሸፈኑን ነው የገለጹት፡፡ በመስክ ምልከታው የፊንጭፍቱ ችግኝ ጣቢያ፣ በሸክላ ቀበሌ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሚላሚሌ የቲማቲም ክላስተር እና ሌሎች የአግሮ ኢንዱስትሪ ሥራዎች ተጎብኝተዋል፡፡

በየዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተለይ ደግሞ በፀጥታ ችግር የተዘጉ መንገዶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሥራት በቅርብ ቀናት ክፍት ለማድረግ እንደሚሠራም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉ መንግሥት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
Next articleበጎጃም ኮማንድፖስት የሚገኘው ክፍለ-ጦር በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ጽንፈኛ ቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ መዉሰዱን አስታወቀ።