የክልሉ መንግሥት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

51

ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ኀላፊዎች ጋር በባሕር ዳር መክረዋል። በምክክሩ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች እና ምሁራን ተገኝተዋል።

በምክክሩ የተገኙ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን አካታች እና አሳታፊ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል። በክልሉ የተባባሪ አካላትን የሥልጠና አሰጣጥ፣ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሠባሠብ ላይ ሊሠሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮችም የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ ጠይቀዋል። በክልሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ እንደሚሠራበትም ተናግረዋል። የከፋ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

አማራ ክልል ያደሩና የነበሩ በርካታ ጥያቄዎች ያሉበት ክልል መኾኑን ገልጸዋል። ጥያቄዎችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊ መኾኑንም ነው ያነሱት። የክልሉ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ታላቅ ተስፋ እንዳለው ገልጸዋል። ለኮሚሽኑ ዓላማ መሳካት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ አሳታፊነት እና አካታችነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። የየአካባቢዎችን ሁኔታ መረዳት እና የታሪክ አረዳድም ትኩረት ይሻል ነው የተባለው። እውነትን እና ነባራዊ ሁኔታን በሚዛናዊነት መረዳት ይገባል ብለዋል። የኮሚሽኑን ዓላማ እና ግብ በሚገባ ለማስረጽ የሚዲያዎች ሚና ላቅ ያለ መኾኑም ተመላክቷል። ምሁራንን እና ሚዲያዎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ተብሏል።

በሕገ መንግሥቱ ላይ አልተሳተፍኩም የሚለው ሕዝብ አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሳይሳተፍ እንዳይቀር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። አሁን ላይ በክልሉ በአብዛኞቹ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ገብቶ መሥራት የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮቹ ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለሥራው ፈተና ኾኖ መቆየቱንም ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር የመፍታት እድል እና አጋጣሚ መኖሩን በማሳየት ሁሉንም አካላት የማሳተፍ እና የማካተት ሥራ ይሠራልም ብለዋል። በግጭት ውስጥ ያሉትንም ጭምር ችግሮችን በውይይት የመፍታት እድል መኖሩን የማሳየት ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በክልሉ ያለውን እውነታ ለማወቅ እና ያለውን አሁናዊ ሁኔታ ለመረዳት ከርእሰ መሥተዳደሩ ጋር ምክክር ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል። በ ፕሮፌሰር መስፍን ከሁሉም አካል አጀንዳን መሠብሠብ ይገባል ብለዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አካታችነት እና አሳታፊነት ዋና መርሁ መኾኑን ያነሱት ፕሮፌሰሩ በኅብረተሰቡ ውስጥ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ሀሳቦችን ማሰራጨት እንደማይገባም አመላክተዋል።

ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያማከለ ሀገራዊ ምክክር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በፖለቲከኞች እና በልሂቃን ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መኾን እንደማይችልም አስታውቀዋል። ሀገራዊ ምክክር ሁሉንም የሚያሳትፍ እና የሚያካትት ነው ብለዋል። ክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር በውይይት ፈትቶ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዝግጁ ለመኾን ምን እየሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሀገራዊ ምክክር የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት በክልሉ የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውቀዋል። የኮሚሽኑን ዓላማ የማስረዳት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። “በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመፍታት የሕዝብ አንድነትን በማጠናከር የምንፈልጋትን ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚገባ ውይይት ተደርጓል” ነው ያሉት። አንድነቱ የተጠናከረ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መልካም እድል እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በተመለከተ እስከ ወረዳ መሪዎች ድረስ የግንዛቤ ፈጠራ መሠራቱን ገልጸዋል። ለኮሚሽኑ ስኬታማነት የግንዛቤ ፈጠራ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል። ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሥልጠናዎች መስጠታቸውንም ተናግረዋል። ለምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማነት የሚደረገው ክትትል መጠናከር እንደሚገባውም ገልጸዋል። የጸጥታው ሁኔታ ለሥራው እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁን ላይ በክልሉ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ ኮሚሽኑ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችልም አመላክተዋል።

የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው አካላት ወደ ሥራው በቅንነት ያለመግባት ችግር መኖርን አንስተዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል። ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የበለጠ መደገፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በአማራ ክልል አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም እንዳለ የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የጸጥታ ችግር አለ በሚል ምክንያት ሥራዎች እንዳይቀሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኀበራት እና ከሌሎች ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚችሉም ገልጸውላቸዋል። የክልሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም አረጋግጠዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ በክልሉ በትኩረት ከሚሠራባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንደኛው መኾኑን አመላክተዋል። ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር በትኩረት ይሠራበታል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረው ክስተት ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ መኾኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleበአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡