
አዲስ አበባ: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ መጋቢት 7/2016 ዓ.ም የተፈጠረውን ክስተት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሠራቸው ሥራዎች እና ባደረገው የደኅንነት ፍተሻ ምርመራ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረው የሲስተም ችግር የሳይበር ጥቃት መኾኑን የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ አለማግኘቱን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።
አሥተዳደሩ ባደረገው ምርመራም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውስጥም ኾነ ከውጭ ለሚደርስበት የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለው እና አስፈላጊውን የሳይበር ደኅንነት ጥንቃቄ እንደሚያደርግ በባንኩ ሲስተሞች ላይ የተደረገው ፍተሻ እንደሚያሳይ ተናረዋል።
ነገር ግን ችግሩ እንዲከሰት ምክንያት የኾኑ ጉዳዮች በምርመራ መለየታቸውን ገልጸዋል። ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲስተም ማሻሻያ በሚያደረግበት ወቅት ቀደም ብሎ ሌላ ሲስተም ማለትም T24 (ኮር ባንኪንግ ሲስተም) ጥቅም ላይ የዋለ የስሌት ሞጁል ወይም አልጎሪዝም በመውሰድ በሞባይል ባንኪንግ ሥርዓት ላይ በቀጥታ ለመተግበር በተደረገ ሙከራ ችግሩ መከሰቱን ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ትዕግስት አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!