
አዲስ አበባ: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)18ኛው ዓመታዊ የቲቢ በሽታ ምርምር ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የቲቢ ቀን “በርግጥም የቲቢ በሽታን መግታት እንችላለን” በሚል መሪ መልእክት እየተከበረ ይገኛል። ቲቢ ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች ዋነኛው ነው። የቲቢ በሽታን ለመከላከል እና ለማከም ኢትዮጵያ የተለያዩ ግቦችን በማስቀመጥ ስትሠራ መቆየቷን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል።
ዶክተር መቅደስ “በሀገሪቱ እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2020 በተሠሩ ሥራዎች የቲቢ በሽታ ስርጭት መቀነስ አሳይቷል” ብለዋል። ኢትዮጵያ የቲቢ ስርጭትን በ2020 ለመቀነስ ግብ ካስቀመጡ ሰባት ሀገራት ውስጥ አንዷ እንደኾነችም አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ፤ በግጭት እና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተፈለገው ደረጃ ለማድረስ ተግዳሮት ኾኖ መቆየቱንም ገልጸዋል ።
በ2023 እ.ኤ.አ 21 ሺህ ዜጎች በቲቢ በሽታ ሕይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል። 156 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቲቢ በሽታ ስለመያዛቸው ተነግሯል። ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2030 የቲቢ በሽታን ብቻ ሳይኾን የቆዳ በሽታን እና ሌሎች ተመሳሳይ በሽታዎችን ለመግታት እየሠራች እንደምትገኝ ዶክተር መቅደስ ተናግረዋል።
ግቡ እንዲሳካ ከዚህ በፊት ከነበረው የምርመራ ዘዴ ዘመናዊ የመመርመርያ ማሽኖችን ለማስመጣት ታቅዷል። ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ እና ሌሎች አጋር አካላት ለዚህ ግብ መሳካት አጋርነታቸውን ገልጸዋል። ጉባኤውን ያዘጋጁት ጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመኾን ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!