በአዲስ አበባ አይቲ ፓርክ ውስጥ የተገነባው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ማዕከል ተመረቀ።

35

አዲስ አበባ: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማበልጸግ በአይቲ ፓርክ ውስጥ የተገነባው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ማዕከል ተመርቋል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኩባንያ (KOICA) ጋር በጋራ ያስገነቡትን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ማዕከል ግንባታው ተጠናቅቆ ነው በዛሬው ዕለት የተመረቀው።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በስታርትአፕ ልማት ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመደገፍ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በተሰጥኦ ማጎልበቻ ማዕከላት ማብቃት አስፈላጊ መኾኑነ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኩባንያ (KOICA) ምክትል ፕሬዚዳንት ኪም ዶንግ ሆ ሀገራቱ ለዘመናት የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያግዙ 20 የተለያዩ ፕሮጀክቶች በKOICA በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡

የስታርትአፕ ሥነ ምህዳሩን ለማስፋትም በአይ ሲ ቲ፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት እና በግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማበልጸግ በዛሬው ዕለት የተገነባው የፈጠራ ማዕከል ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል። ማዕከሉ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች በውድድር ተለይተው አዋጭ ሃሳቦቻቸው ወደ ቢዝነስ የሚቀየርበት የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ መያዙን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባሕር ዳርን ጽዱ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጎብኚዎችን የምትስብ ለማድረግ እየተሠራ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleኢትዮጵያ ዘመናዊ የቲቢ መመርመሪያ ማሽኖችን በማስገባት በ2030 እና በ2035 የቲቢ በሽታን ለመግታት ግብ አስቀምጣ እየሠራች እንደኾነ ተገለጸ።