
ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚንስትር ጫልቱ ሳኒ በ2016 በጀት ዓመት በባሕር ዳር ከተማ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን አስጀምረዋል። በበጀት ዓመቱ ሊገነቡ ከታቀዱት መካከል በሦስት ክፍለ ከተሞች የሚገነቡ የጠጠር መንገዶችን ነው ሚንስትሯ ያስጀመሩት።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ልማት ሥራ አስኪያጅ ተሻገር አዳሙ በከተማዋ ከ2015 በጀት ዓመት የዞረ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ በ962 ሚሊየን ብር በጀት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ዛሬ የተጀመረው 4 ነጥብ 56 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት በ93 ነጥብ 72 ሚሊየን ብር በጀት የሚሰራ መኾኑን ተናግረዋል። በከተማዋ በ2016 በጀት ዓመት 11 ፕሮጀክቶችን ለማከናወን 1 ቢሊየን 483 ሚሊየን 893 ሺህ ብር መመደቡንም አቶ ተሻገር ገልጸዋል።
የመንገድ ግንባታው በተጀመረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ሠፈራችው መንገድ ስለሌለው በተለይ በክረምት በጣም እንደሚቸገሩ አውስተው መንገዱን ለመሥራት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ተጀምሮ እንዳይቀር እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማ መሠረተ ልማት ማሟላት እና ውበቱን መጠበቅ ለነዋሪዎቹ ምቹ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ መኾኑን ገልጸዋል። “ባሕር ዳርን ጽዱ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጎብኚዎችን የምትስብ ለማድረግ እየተሠራ” መኾኑንም ተናግረዋል።
”ባጋጠመን የሰላም ችግር ምክንያት ሥራዎቻችን ባቀድነው ልክ ለመጀመር ባንችልም አኹን ላይ ግን በጸጥታ ኃይሉ ርብርብ የከተማው ጸጥታ በመመለሱ ልማቱን ለመቀጠል ችለናል” ያሉት ከንቲባው ልማት የተጀመረው በሰላም ላይ መኾኑን እና ለሰላሙ ደግሞ የመከላከያ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሉ ርብርብ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። የሕዝቡ ቀና ትብብርም አይተኬ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተጀመረው መንገድ ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በቀጣይም የመንገዶችን ደረጃ የማሳደግ እና ውበታቸውን የመጠበቅ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል። የፌዴራል ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚንስትር ጫልቱ ሳኒ ከተሞችን የማልማቱ ሥራ ትኩረት የተሰጠው እና ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑን ጠቅሰው ዛሬ የምናስጀምረው የመንገድ ግንባታም የዚሁ የከተማ ልማቱ አንዱ አካል ነው ብለዋል።
መሠረተ ልማት ለማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ልማት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰው መንግሥት ልማቱን ሲሠራ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ከማኅበረሰቡ እንደሚጠበቅ ሚንስትሯ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!