
ጎንደር: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በሕዝብ የተሰጣቸውን ኀላፊነት ባልተወጡ 21 የሥራ ኀላፊዎች ላይ አሥተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የጎንደር ከተማ መካከለኛ እና ጀማሪ አመራሮች ያለፋት ስምንት ወራት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫ ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩ አቡሃይ ባለፋት ወራት በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ መንግሥት ለመሥራት ያሰባቸውን የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎችን ለመከወን አስቸጋሪ አድርጎበት መቆየቱን ገልጸዋል። የፓለቲካ አመራሩ፣ ሕዝቡ እና የጸጥታ መዋቅሩም አሁን ለተገኘው አንፃራዊ ሰላም የራሱን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም በርካታ ሥራዎች መሠራት ያለባቸው በመኾኑ የአመራሩን አንድነት ማጠናከር የመጀመሪያ ተግባር ሊኾን እንደሚገባ አንስተዋል። አሁንም በመንግሥት በኩል የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸው በቀጣይም የጸጥታ እና የልማት ሥራ አመራሩ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
አሁንም ያለውን አለመረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕዝቡ እንዲንገላታ በሚያደርጉት ላይ ተጠያቂነት ማምጣት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል። የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው ያለፈውን ጊዜ በመረዳት ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣ በማድረግ በኩል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ መድረኩ ጉድለቶችን ለማሳየት እንዲሁም ለማየት ይጠቅማል ነው ያሉት።
ያለፋት ወራት የተሠሩ ሥራዎች የሚገመገሙበት እና ኅብረተሰቡ የሰጠው የቤት ሥራ ምን ላይ ነው የሚለው ውይይት እንደሚደረግበት አቶ ቻላቸው ተናግረዋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በሕዝብ የተሰጣቸውን ኀላፊነት ባልተወጡ 21 አመራሮች ላይ አሥተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም የፓርቲ ኀላፊው ገልጸዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ የኾኑ መካከለኛ እና ጀማሪ አመራሮችም ሥልጠናው መሰጠቱ በኅብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት። በከተማ አሥተዳደሩ ለሚገኙ 234 መካከለኛ እና ጀማሪ አመራሮች የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ- ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!