
ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተጀመረበትን ቀን በምሥጋና እንደሚከበር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ግዙፍ የኾነውን ግድብ በራስ አቅም በመገንባት ራስን በራስ ማልማት እንደሚቻል ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መኾን ችለዋል፡፡ “የሕብረ ብሔራዊቷ ኢትዮጵያ ግዙፍ አሻራ” ዳር ሊደርስ ተቃርቧል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ 13ኛ ዓመት ሊሞላው ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ በ13 ዓመት ጉዞው የግድቡ ግንባታ 95 በመቶ መድረሱን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ቀሪ ሥራውም በሰባት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጽሕፈት ቤቱ ገልጾ ነበር፡፡
ቀሪ ሥራውን ለማጠናቀቅ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸውልናል፡፡ እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም ከ743 ሚሊዮን 487 ሺህ ብር በላይ ተሠብሥቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚኾነው ገቢ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ የተገኘ ነው፡፡
በቀሪ ወራት በተጠናከረ መንገድ ለመሠብሠብ እየተሠራ ይገኛል ብለዋ፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት ደግሞ ከ18 ቢሊዮን 973 ሚሊዮን ብር በላይ ከማኅበረሰቡ መሠብሠብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ግድቡ የተጀመረበትን ቀን አስመልክቶ በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ በመርሐ ግብሩ የሥዕል ኢግዚቪሽን፣ ቦንድ የገዙ ሰዎች መልዕክት እና የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡
ፕሮጀክቱ እውን እንዲኾን በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን 40 በመቶ የሚኾነውን የኤሌክትሪክ ሽፋን ወደ 75 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!