
ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወራሚት አትክልት እና ፍራፍሬ ምርምር እና ሥልጠና ንዑስ ማዕከል በሄክታር እስከ 12 ኩንታል ዘር እና 350 ኩንታል ኮረት የሚሰጥ የሽንኩርት ዘር ዝርያን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ ነው፡፡ በክረምት መመረት የሚችል የቀይ ሽንኩርት ዝርያን ወደ አርሶ አደሮች ለማድረስ የዘር ብዜት ሥራ እያከናወነ መኾኑን የወራሚት አትክልት እና ፍራፍሬ ምርምር እና ሥልጠና ንዑስ ማዕከል አስታውቋል፡፡
ንዑስ ማዕከሉ እያከናዎናቸው የሚገኙ የምርምር ሥራዎችን ለባለድርሻ፣ አጋር አካላት እና ለአርሶ አደሮች አስጎብኝቷል፡፡ በመስክ ጉብኝቱ በመኸር ወቅት መመረት የሚችሉ የቀይ ሽንኩርት ዝርያዎችን በማላመድ የተሻለውን በመለየት የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ንዑስ ማዕከሉ ገልጿል፡፡
በንዑስ ማዕከሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ተመራማሪ ምንየለት ጀምበሬ በመኸር የሚመረቱ የቀይ ሽንኩርት ዝርያዎችን በማላመድ “ናፊስ” የተሰኘው ዝርያ የተሻለ ምርት የሚሰጥ መኾኑ በመረጋገጡ ለአርሶ አደሮች ተዋውቋል፡፡ በጅአይዜድ ፕሮጀክት በጀት ድጋፍ በማዕከሉ ግቢ ውስጥ የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ዝርያው በሄክታር እስከ 12 ኩንታል ዘር እና 350 ኩንታል ኮረት የሚሰጥ መኾኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ተመራማሪው የመትከያ ወቅት የመወሰን ጥናት መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡ ይህ በመኸር መመረት የሚችል የቀይ ሽንኩርት ዝርያ የተሻለ የዘር ምርት እንዲሰጥ ከተፈለገ በጥቅምት ወር መጨረሻ እና በህዳር ወር መጀመሪያ መተከል ያለበት ሲኾን በቆጋ፣ ደራ፣ ፎገራ አካባቢዎች እና መሰል ሥነ-ምህዳሮች ላይ በስፋት መመረት እንደሚችል ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
መረጃው የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!