
ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ኀላፊዎች ጋር እየመከሩ ነው። በምክክሩ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች እና ምሁራን ተገኝተዋል።
ርእስ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባር በክልሉ በምን መልኩ እየተከናወነ እንደኾነ፣ በቀጣይስ ምን ዓይነት አቅጣጫ መቀመጥ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ይመከራል ነው ያሉት። ለአሁን ብቻ ሳይኾን መጻዒ እድል የሚወስኑ ጥያቄዎች ያሉበት ክልል እና ሀገር መኾኑንም ተናግረዋል። በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሃሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሚፈለገው ፍጥነት ልክ ሳይሠራ መቆየቱንም አመላክተዋል።
አሁን ላይ ክልሉ በተሻለ የሰላም እንቅስቃሴ ላይ መኾኑንም ገልጸዋል። የኮሚሽኑ ተግባራት በአግባቡ እንዲፈጸም የራሳችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባናል ነው ያሉት። የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማበርከትም ዝግጁ ነን ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። የኮሚሽኑ ዓላማ እና ግብ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መኾኑንም አንስተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ግጭት የከተተዉን እና የማያግባባውን ችግር አጀንዳ በመቅረጽ እና ምክክር በማድረግ ወደ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው ብለዋል። የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ሥራ የሀገሪቱን ሁሉንም አካባቢዎች ማዳረስ እና ችግሮችን መለየት መኾኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ለመድረስ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ መሥራታቸውንም ገልጸዋል።
ከፍተኛ አለመግባባቶች ባሉባት ሀገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራን መቋጨት እንደማይቻልም ተናግረዋል። የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ባለድርሻ አካላት መኾናቸውንም ገልጸዋል። የኮሚሽኑ ዋናው መርሕ አካታች እና አሳታፊ ምክክር ማድረግ መኾኑንም ተናግረዋል። በየወረዳዎች ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየተጠናቀቀ መኾኑንም አመላክተዋል። ተሳታፊ ልየታ ሲጠናቀቅ ቀጣይ ሥራ አጀንዳ መሰብሰብ እንደሚኾንም ገልጸዋል።
የአጀንዳ ስብሰባው ከተካሄደ በኋላ አጀንዳ የመቅረጽ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በሀገር ደረጃ ወደ ጦርነት እና ቅያሜ ያስገቡ አጀንዳዎች ትኩረት እንደሚደረግባቸውም ገልጸዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕውቀት እና በርካታ ውይይቶችን እንደሚጠይቅም አመላክተዋል። ከአማራ ክልል መሪዎች ጋር የሚደረገው ምክክር ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ለመፈጸም እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ሥራውን በአግባቡ ለመፈጸም ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል። ሚዲያዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስኬታማነት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!