
ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚገነባው የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአካባቢው ተጨማሪ ሃብት ለማመንጨት እና ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል እንደኾነ የፍትህ ሚኒስትሩጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ተናገሩ፡፡
በፍትህ ሚኒስትሩ የተመራው የፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን ምልከታ ካደረገባቸው ፕሮጀክቶች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ሃሳብ አመንጪነት ከሚከናወኑ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል የጎርጎራ ፕሮጀክት አንዱ ነው። የሱፐርቪዥን ቡድኑ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተከናወኑ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ዛሬ ገምግሟል፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዎስ (ዶ.ር) በግምገማ መድረኩ ላይ እንደገለጹት “የጎርጎራ ፕሮጀክት አካባቢውን በልማት ለማስተሳሰር የሚያግዝ ነው” ብለዋል። ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ጸጋዎችን ይዞ የመጣ በመኾኑ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአካባቢውን መዋቅራዊ ፕላን በማሻሻል በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማሳተፍ በሪል ስቴት፣ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የማእከላዊ ጎንደር ዞን የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን በጉብኝታቸው ወቅት መመልከታቸውን ተናግረዋል። ቡድኑ ባካሄደው የመስክ ግምገማ ላይ በመመሥረትም ጠንካራ ጎኖች እንዲቀጥሉ እና ድክመቶች እንዲታረሙ አቅጣጫ የሰጠ ሲኾን በቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግም አመልክተዋል።
የማእከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ይዞት የመጣውን ጸጋ አስፍቶ ለመጠቀም ከጎንደር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጎርጎራ ከተማ ማስተር ፕላን ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡ እንደ ኢዜአ ዘገባ ቡድኑ በዞኑ ተገኝቶ የልማት እና የሰላም እንቅስቃሴውን መመልከቱም በቀጣይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የቡድኑ አባል እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የአካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች በማስተሳሰር ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!