ሰላምን ለማጽናት የሃይማኖት ተቋማት ፊታውራሪ ሊኾኑ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

21

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላምን ለማጽናት እና በመልካም ስብዕና የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሃይማኖት አባቶች ሚና መጠናከር እንደሚገባው የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የመቻቻልና የአብሮ መኖር እሴቶች መገለጫ ስትኾን የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ግጭትን የሚፈቱበት ባሕል ለሀገር ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መኾኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያውያንን ባሕል እና ወግ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚገኙ መልካም እሴቶችን የሚያከብር ትውልድን በማፍራት ረገድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል። በተለይም መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ ከመቅረጽ አኳያ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱት መካከል ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና የሃይማኖት ተቋማት ዋነኞቹ እንደኾኑ የሃይማኖት አባቶች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ኀላፊ መጋቢ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ በሀገሪቱ የሚገኙ የእምነት ተቋማት መልካም ስብዕናን የተላበሰ ትውልድን ከመቅረጽ አንጻር ብዙ ሥራዎችን ቢሠሩም በቂ ነው ማለት ግን አያስደፍርም ብለዋል።
በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ መልካም እሴቶችን የሚጥሱ የሉም ማለት አይቻልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ እና የሃይማኖት መምህር ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ትውልዱን በጥሩ ሰብዕና ማነፅ ላይ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል። ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ እና በመቅረጽ ላይ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ተዋናዮች ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።

ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሟትን ችግሮች እንድትሻገር የሃይማኖት አባቶች እና ተቋማት ትውልድ የመገንባት ሚናቸውን ሊያሳድጉ፤ ወጣቱም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በሀገሪቱ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ሀገሩን የሚወድድ ለሌሎች ቀና የኾነ ሰው በሚፈለገው ደረጃ አለማፍራታቸው ሀገሪቱን ለፈተና እየዳረጋት ይገኛል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ናቸው። አሁን ላይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መልካም ሥነ ምግባር ያለውን ትውልድ ለማፍራት ያሉበትን ክፍተቶች በመሙላት ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ሀገሪቱን ከችግር ማላቀቅ አዳጋች እንደኾነም አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሐይሸንጌን ለመስኖ መጠቀም ነውር ነው እንባል ነበር ” በወፋላ ወረዳ የአዲጎሎ ቀበሌ አርሶ አደሮች
Next article“የጎርጎራ ፕሮጀክት አካባቢውን በልማት ለማስተሳሰር የሚያግዝ ነው” ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር)