
ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወፍላ ወረዳ አዲጎሎ ቀበሌ በበጋ መስኖ የለማ የስንዴ ክላስተር በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች እና የወረዳ ሥራ አሥፈጻሚዎች ተጎብኝቷል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ክላስተር በማልማታቸው ተጠቃሚ መኾናቸውን በወፍላ ወረዳ አዲጎሎ ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተናግረዋል። በአዲጎሎ ቀበሌ 100 በላይ አርሶ አደሮች 29 ሔክታር በላይ መሬት የሐይሸንጌ ሐይቅን በመጠቀም በበጋ መስኖ ስንዴ በኩታገጠም እያለሙ ነው።
“ለበርካታ ዓመታት ሐይሸንጌ ሐይቅን እንዳንጠቀም ጨዋማ ነው እንባል ነበር። ሐይሸንጌን ለመስኖ መጠቀም ነውር ነው እንባል ነበር ። “አሁን ግን መንግሥት ባደረገልን የማዳበሪያ እና ጀኔሬተር ድጋፍ ተነሳስተን በማልማታችን የተሻለ የሰብል ቁመና አለ። በዚህም ተጠቃሚ እንኾናለን ሲሉ አርሶ አደር ካህሳይ ኩርፋይ ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ዘርዓይ ካህሳይ በበኩላቸው የቀበሌውን ሕዝብ በመቀስቀስ በበጋ መስኖ ሐይሸንጌ ሐይቅን እንድንጠቀም ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሥራታችን ለውጥ አይተናል ብለዋል። ከ3 ሄክታር ማሣ እስከ መቶ ኩንታል ምርት ድረስ እንደሚጠብቁ ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በክረምት ወቅት በሄክታር ከሰባት እስከ ስምንት ኩንታል ያገኙ እንደነበር ያወሱት ደግሞ አርሶ አደር ዝናቡ ደመቀ ናቸው። “በበጋ መስኖ የለማው ስንዴ አይደለም በበጋ በክረምት አይተነው አናውቅም” ብለዋል፡፡ አርሶ አደሩ መንግሥት የማዳበሪያ፣ የጄኔሬተር እና የምርጥ ዘር ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል፡፡
የወፍላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ታፈረ በወረዳው 200 ሄክታር መሬተት በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዶ 244 ሄክታር መሬት መልመቱን ገልጸዋል። በሄክታር 35 ኩንታል በአጠቃላይ ከ11 ሺህ በላይ ምርት ይገኛል ብለን አቅደናል ያሉት አቶ አብርሃም 2 ሺህ 820 በላይ አርሶ አደሮች የዚህ ፖኬጅ ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል።
የሐይሸንጌ ሐይቅን ከዓሣ ምርቱ በተጨማሪ ለአርሶ አደሮች በበጋ መስኖ እንዲያገለግል ለማድረግ የሠራነው የግንዛቤ ማስጨበጣ ሥራ ውጤታማ ነበር ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ በበኩላቸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 937 ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደን 590 ሄክታር መሬት በስንዴ ክላስተር ማልማት ችለናል ብለዋል።ይህም የእቅዳችንን 62 በመቶ አከናውነናል ነው ያሉት።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ዋግን ከችግር ለማላቀቅ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መጠናከር አለበት ብለዋል። በቀጣይ ከበጋ ወቅት አፈጻጸም ተሞክሮ በመውሰድ ዋግ ኽምራን ከችግር ለማውጣት በክረምትም በኩታገጠም ማልማት እንደሚገባ በጉብኝቱ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ