የተከሰተው ጸጥታ ችግር የታቀደውን የሥራ እድል ለመፍጠር እንቅፋት መኾኑን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ገለጸ።

60

ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በዕውቀት እና ክህሎት የዳበረ እና ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው። ባለፉት ወራት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተቋሙ ላይ ጉዳት ማድረሱን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ገልጸዋል።

በክልሉ ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ያለውን የመረጃ አያያዝ ችግር ለመፍታት የዲጅታላይዜሽን ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ቢሮ ኀላፊው አስረድተዋል። ይሁን እንጅ ከ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ጽንፈኛው ቡድን በክልሉ በፈጠረው ችግር ምክንያት የቢሮው እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መፈተኑን ገልጸዋል።

በዚህም በ2016 በጀት ዓመት የሥራ እድል ለመፍጠር ከታቀደው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ማሳካት የተቻለው 39 በመቶ ብቻ ነው። ለማደራጀት ከታቀደው 68 ሺህ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ ደግሞ ማሳካት የተቻለው 20 በመቶ ብቻ ነው። ቢሮ ኀላፊው በመግለጫቸው እንደጠቆሙት:-
👉 ከ126ቱ የመንግሥት ኮሌጆች ውስጥ 23ቱ በጸጥታው ችግር ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደታቸው ተቋርጧል።

👉 ከ110 የግል ኮሌጆች ውስጥ 19ኙ ሥራ አቁመዋል።

👉 በዚህ ዓመት በመንግሥት እና በግል ኮሌጆች ይማራሉ ተብሎ በእቅድ ከተያዙት 205 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 29 በመቶ ብቻ ናቸው በመማር ላይ የሚገኙት።

👉 128 የሥራ እና ሥልጠና ተቋማት በጽንፈኛው ቡድን ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል ብለዋል ዶክተር ስቡህ

የቢሮው ባለሙያዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የሥራ እድል ለመፍጠር እና በሥራ ላይ ያሉትንም ለመደገፍ እንቅፋት ገጥሟቸዋል ሲሉም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። አንገብጋቢ የኾነውን የወጣቶች የሥራ እድል እጦት ችግር ለመቅረፍ ሰላም የማይተካ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል። በመኾኑም ክልሉን ከገባበት ችግር በዘላቂነት ማውጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገነቡ ተገለጸ።
Next article“ሐይሸንጌን ለመስኖ መጠቀም ነውር ነው እንባል ነበር ” በወፋላ ወረዳ የአዲጎሎ ቀበሌ አርሶ አደሮች