በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገነቡ ተገለጸ።

107

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገነቡ ተገልጿል። ይህ የተባለው ሄልቬታስ ኢትዮጵያ እና ብሪጅስ ቱ ፕሮስፐሪቲ የተንጠልጣይ ድልድይ ቴክኖሎጂ ግንባታ እና ጥገና በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ሥልጠና በማስጀመር ሥነ ሥርዓት ላይ ነው። ሥልጠናው በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደሚጀምር ነው የተገለጸው። በቀጣይ በሌሎች ኮሌጆች እንደሚሰጥም ተመላክቷል።

ሥልጠናው የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ ግንባታዎችን እና ጥገናዎችን በራስ አቅም ለማከናወን ያስችላል ነው የተባለው። የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታዎች በመሠረተ ልማት ተገልለው የቆዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማገናኘት ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል። በተደጋጋሚ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችንም ይፈታል።

የሄሌቬታስ ኢትዮጵያ ተንጠልጣይ ድልድይ ፕሮጄክት ሥራ አሥኪያጅ ተስፋሁን ሞላ ሄልቬታስ ዜጎች በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር፣ የሴቶች ጫና እንዲቀንስ፣ ፍትሐዊነት እና እኩልነት እንዲረጋገጥ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ዜጎች ተፈጥሮን በእኩልነት እና በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙ እንደሚሠራም አመላክተዋል። የዜጎች መብት እንዲከበር እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ይሠራልም ተብሏል።

ውጤት ላይ መሠረት ያደረገ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ይሠራል ነው የተባለው። ባለፉት ዓመታት የተንጠልጣይ ድልድይ ሲሠሩ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል። በክልሉ አሁን ላይ ጥሩ የኾነ የተንጠልጣይ ድልድይ ልምድ እየተገኘ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ተንጠልጣይ ድልድይ በመሥራታቸው ማኅበረሰቡ የተንጠልጣይ ድልድይ እንዲሠራለት እንዲጠይቅ፣ መንግሥትም ለተንጠልጣይ ድልድይ ትኩረት እንዲያደርግ ማድረጉንም ገልጸዋል። በሄልቬታስ ኢትዮጵያ በተሠሩ 21 የተንጠልጣይ ድልድዮች ከ354 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ ቴክኖሎጂ በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ በኮሌጆች መሰጠት በዘርፉ በቂ የሰው ኀይል እንዲፈጠር እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ፣ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ይዞ እንዲያሥተዳድር በማድረግ በኩል ችግሮች እየገጠሟቸው መኾኑንም ገልጸዋል። የባሕርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ፈለቀ ውቤ ሥልጠናው የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እና ብቁ የሰው ኀይል እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ሥልጠናው የራሱ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል። ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጁ ተንጠልጣይ ድልድዩን በበቂ ሁኔታ መሥራት እንደሚችልም አመላክተዋል። ሥልጠናው የኮሌጆችን አቅም እንደሚያሳድግም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ሄልቬታስ ለጀመረው ሥራ ቢሯቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ሥራው ውጤታማ እንዲኾን ወጣቶችን አደራጅቶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋል ነው ያሉት። የሥራና ሥልጠና ቢሮ የሠለጠነ እና አዕምሮው የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚሠራም አመላክተዋል። ሥርዓተ ትምህርት እና ሥልጠናው ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የተንጠልጣይ ድልድይ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ተጠቃሚ እንዲኾን ቢሮው የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። ሄልቬታስ ዜጎችን በድልድይ ከማገናኘት ባለፈ የሥራ እድል እንዲፈጠር እያገዛቸው መኾኑንም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ሄልቬታስ ኢትዮጵያ በክልሉ ከሁለት ዓመታት በላይ ሥራ እየሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል። በእነዚህ ዓመታት 21 የሚደርሱ ተንጠልጣይ ድልድዮችን መሥራቱንም አስታውቀዋል። በ2016 በጀት ዓመት 24 ተንጠልጣይ ድልድዮችን እየሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት። ድርጅቱ በአማራ ክልል እየሠራው ያለው ሥራ ዘርፈ ብዙ መኾኑንም አስታውቀዋል። የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮችን እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ሥራው በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች መደገፉ ጥሩ አጋጣሚ መኾኑንም ነው የተናገሩት። ሥራዎችን በትኩረት መሥራት ከተቻለ ለክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል። መንገድ ቢሮው በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ210 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው” የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ
Next articleየተከሰተው ጸጥታ ችግር የታቀደውን የሥራ እድል ለመፍጠር እንቅፋት መኾኑን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ገለጸ።