
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሳትጎርስ የምታጎርሰው፣ ሳትለብስ የምታለብሰው፣ ሳትጠጣ የምታጠጣው፤ ከራሷ በላይ ለልጆቿ የምትጨነቀው፣ ወገቧን አስራ ስትብከነከን ውላ ያለ እንቅልፍ የምታድረው እናት ፈተናዋ ብዙ ነው፡፡ ልጆቿ ሲስቁላት ትስቃለች፣ ልጆቿ በከፋቸው ጊዜ አብዝታ ትከፋለች፡፡ ሲርባቸው ትራባለች፤ በጥጋባቸው ትጠግባለች፣ በእርካታቸው ትረካለች፤ በጥማቸው ትጠማለች፣ በእርዛታቸው ትታረዛለች፡፡ በሕመማቸው ትታመማለች፡፡ በሞቱባትም ጊዜ አብዝታ ታለቅሳለች፤ ማቅም ትለብሳለች፡፡
የወለዱት ባልወለድን፣ ያረገዙት ባላረገዝን የሚሉበት ዘመን መጣባቸው እና ፈተናው በዛባቸው፡፡ ስለ ምን ቢሉ አርግዘው ለመውለድ፤ ወልደው ለማሳደግ ተቸግረዋልና፡፡ የሰላም እጦት የበዙ እናቶችን ፈተናቸው፤ ልጆቻቸውን እየነጠቀ አስለቀሳቸው፣ እድለኛ ኾነው ልጆቻቸውን ያልተነጠቁትም እንነጠቅ ይኾን የሚል ስጋት ሀሳብ አበዛባቸው፤ ጭንቅ ፈጠረባቸው፡፡
በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ብዙዎች እርግዝናቸውን መከታተል ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ብዙዎች በቤት ውስጥ ወልደዋል፤ ሕጻናት ክትባት አጥተው ቀርተዋል፡፡ ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ነው፡፡ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን ትተነዋል፡፡ በቅርቡ ሦስተኛ ልጃቸውን ተገላግለዋል፡፡ በአካባቢው የተፈጠረው የሰላም እጦት የቅድመ ወሊድ ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ አድርጎባቸው እንደነበር ነግረውናል፡፡ “ክትትል ለማድረግ በቀናችን ለመምጣት ስንፈልግ መምጣት አንችልም ነበር፡፡ ዛሬ ውጊያ አለ፣ ዛሬ መንገድ ይዘጋል ስለሚባል በአግባቡ መከታተል አልቻልንም” ነው ያሉት፡፡
ምጥ በሌሊት የሚመጣባቸው እናቶች ወደ ሕክምና ተቋማት አይሄዱም፡፡ በቤታቸው ይወልዳሉ፡፡ አምቡላንሶች እና ሌሎች ተሸከርካሪዎች በነጻነት አይሠሩም፡፡ እናቶችም ስጋት ስላለባቸው፣ ከምጡ ይልቅ የሚገድለን ሌላ ነገር መንገድ ላይ ይጠብቀናል ስለሚሉ አይሄዱም፡፡ “አጋጣሚ ኾኖ ቀን ኾነና በሰላም ተገላገልኩ፡፡ ምጥ ማታ የመጣባቸው እናቶች ከቤት ነው የወለዱት፡፡ እኔም ማታ መጥቶ ቢኾን አልሄድም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሲረዳኝ ቀን ላይ ኾነልኝ፡፡ ማታ ከኾነ ቤት ይወለዳል እንጂ አይወጣም” ይላሉ፡፡
በሰላሙ ጊዜ የነበረውን የወሊድ ክትትል እና በሰላም እጦት ውስጥ ያለውን ክትትል እያነጻጸሩ ሲነግሩን “ በሰላሙ ጊዜ ወደ ጤና ተቋማት ስንሄድ ባለሙያዎቹ ደስተኞች ናቸው፡፡ ደስ ብሏቸው ይንከባከቡናል፡፡ እኛም ደስ እያለን እንሄዳለን፤ አሁን ግን እነርሱም በስጋት ውስጥ ስለሚሠሩ ይቸገራሉ፡፡ ይህም ቢኾን እናመሠግናቸዋለን፡፡ ከእግዚአብሔር በታች እነርሱን አምነን ነው የምንመጣው፡፡ ቅስማቸው ተሰብሯል፡፡ የመጀመሪያ ልጄን ማታ ላይ ነበር የተገላገልኩ እንክብካቤው የሚገርም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ብዙ ልዩነት አለው፡፡ እኛም ይጨንቀናል፤ እነርሱም ይጨንቃቸዋል፤ ምክንያቱም በዚያች ሰዓት የሚመጣው ነገር አይታወቅም፡፡ ለእኛም ለእነርሱም ስጋት አለ” ነው ያሉን፡፡
የጸጥታ ሁኔታው ለእናቶች ጤና አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ምን ይፈጠር ይኾን እያሉም ስጋታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ለወትሮው አምላኬ እንኳንም ዘር ሰጠኸኝ በሰላም እንደጸነስኩ በሰላም አገላግለኝ ይሉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ስለ ምን አረገዝን አሉ፡፡ ይሄም መጸነሳቸውን ጠልተው አልነበረም፡፡ ችግሩ አርግዞ ለመውለድ፣ ወልዶ ለመሳም አልኾን ብሏቸው ነው እንጂ፡፡
እኒህ እናት በተገላገሉበት የጤና ተቋም በነርስ ሙያ አገልግሎት የሚሰጡት ባለታሪካችን ደግሞ ያሳለፉት ጊዜ ፈታኝ እንደነበር ነግረውናል፡፡ አሁንም ፈተናውን ሙሉ ለሙሉ አልተሻገርነውም ነው ያሉት፡፡ እናቶች እንደበፊቱ የቅድመ ወሊድ ክትትላቸውን በአግባቡ አያደርጉም፡፡ መድኃኒትም በበቂ ሁኔታ አይገኝም ነው ያሉን፡፡
“በፊት ቀንም ይሁን ማታ የአምቡላንስ እና የባጃጅ አገልግሎት አለ፡፡ አሁን ግን አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ምክንያቱም ስጋት ስላለ ይፈራሉ፡፡ ከአቅም በላይ የኾነውን ወደ ተሻለ ሕክምና ለመላክም አስቸጋሪ ነበር፡፡ እናቶችም እዚሁ እንሞታለን እንጂ አንሄድም፤ ሰው ጨምረን አንገድልም ይሉናል፡፡ ያለንበት ወቅት እጅግ ፈተና ነው፡፡ እኛም እንፈራለን፣ እነርሱም ይፈራሉ፤ አገልግሎት እየሰጠን ነው፤ ነገር ግን ከባድ ነው ” ይላሉ፡፡
ጊዜው ለታካሚዎች ብቻ አይደለም፡፡ ለአካሚዎችም እጅግ ፈተና ነው፡፡ በነጻነት ሙያዊ ግዴታን ለመወጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ “ሰላም እንዲመጣ እንፈልጋለን፤ ጤና ጣቢያ አንድም ቀን አልዘጋንም፤ ስጋቱ ግን ከባድ ነው፡፡ እንደ ድሮው እናቶችን እንድናገለግል፤ ደስ ብሎን እንድንቀበል ሰላም እንፈልጋለን፤ አሁን ላይ ተሳቀን ነው አገልግሎት የምንሰጠው፤ በተለይ ማታ ላይ እንደምንም ብላ አንዲት ወላድ እናት ስትመጣ ወጥተን ለማገልገል በጣም ነው የምንፈራው፤ ሰላም እንዲኾን ሁሉም የቤት ሥራ አለበት” ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ቅድመ ወሊድ ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአራተኛ ቅድመ ወሊድ ክትትል ከ36 በመቶ በላይ የሚኾኑ ነፍሰጡር እናቶች ክትትል አላደረጉም ብለዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ በእናቶች ጤና ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው እስከመጨረሻው ድረስ የቅድመ ወሊድ ክትትል እንዳያደርጉ እያደረጋቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
እናቶች በሠለጠነ ባለሙያ ታግዘው በጤና ተቋማት እንዲወልዱ እንደሚፈለግ የተናገሩት ኀላፊው በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት 44 በመቶ የሚኾኑ እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ መገደዳቸውንም አንስተዋል፡፡ በቤት ውስጥ መውለድ ለእናቶች ሕይወት አደጋ እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡
ለእናቶች የጤና አገልግሎት ለመስጠት አምቡላንሶች እንደሚያስፈልጉ ያነሱት ኀላፊው በተፈጠረው ችግር ምክንያት 124 አምቡላንሶች ላልታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡ አምቡላንሶች ከአሽከርካሪዎች መነጠቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ አምቡላንሶች ላልተገባ ዓላማ መዋላቸው ደግሞ የተሳካ የእናቶች እና የሕጻናት የጤና አገልግሎት ለመስጠት ፈታኝ እንደኾነባቸው ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕጻናት ወደ ጤና ተቋማት መጥተው እንዳይታከሙ እንዳደረጋቸውም አንስተዋል፡፡ ምንም አይነት ክትባት ያላገኙ ሕጻናት መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሰባት ወራት ውስጥ ክትባት ጀምረው ያላጠናቀቁ 14 በመቶ ሕጻናት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በእናቶች እና በሕጻናት ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯልም ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በእናቶች እና በሕጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ተገንዝቦ ከዚህ ችግር እንዴት ነው መውጣት የምንችለው የሚለውን ማሰብ፣ ማስተካከል፣ ሰላማዊ አማራጮችን መምረጥ አለበት ብለዋል፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የተለያዩ መድኃኒቶች እና የጤና ቁሳቁሶችን ለማሰራጨት ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡ መድኃኒቶችን እና የጤና ቁሳቁስ ለማሰራጨት በሚደረገው ሥራ መኪናዎች እንደሚታገቱ እና እንደሚዘረፉም ገልጸዋል፡፡ ሕጻናትን ለመታደግ የሚሠራጩ መድኃኒቶችም እንደሚዘረፉ ተናግረዋል፡፡
ግጭት ባለባቸው አካበቢዎች መድኃኒቶችን እና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁስ ለማድረስ መቸገራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት እንዳይቋረጥ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ኀላፊው የጤና ባለሙያዎችም ከፍተኛ የኾነ ጫና እየደረሰባቸው መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ቤት ለቤት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ገልጸዋል፡ ማኅበረሰቡ የራሱን ተቋማት መጠበቅ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሰላማዊ አማራጮችን መከተል ይገባዋል ያሉት ኀላፊው ሰላም ለጤና ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ እርስዎስ ስለ ሰላም ምን አይነት አስተዋጽዖ ያደርጉ ይኾን? ሰላም ከሌለ እናቶችን ያሳጣልና፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!