”የከተሞች ችግር መዋቅር በመዘርጋት እና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ብቻ አይፈታም” የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

60

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በየደረጃው ከሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ጋር የልማት እና መልካም አሥተዳደር ጉዳዮችን በመገምገም የ60 ቀናት የእቅድ ኦሬንቴሽን አካሂዷል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋ የገጠማትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማስተካከል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ለመጀመር እና በታቀደው ልክ ለመፈጸም ርብርብ መደረጉን ገልጸዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሁን ላይ የከተማው ልማት ከማይደናቀፍበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል። የተገኘው ሰላምም የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ እና የከተማው የጸጥታ መዋቅር ባደረጉት ርብርብ የተገኙ መኾኑን ተናግረዋል። አመራሩም ሕዝቡ የሰላሙ ደጋፊ እንዲኾን ያደረገው ጥረት አጋዥ እንደኾነ ጠቁመዋል።

የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር፣ የኑሮ ውድነት እና የሥራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን የጠቀሱት ከንቲባው የሚደረገው ውይይትም የተገኘውን ሰላም በማዝለቅ እና የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ የ60 ቀናት የጋራ እቅድ መኾኑን ገልጸዋል። በውይይቱ የተሳተፉት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ የፌዴራል መንግሥት የልማት እቅድ በማቀድ ክልሎችም እንደየራሳቸው ሁኔታ አቅደው የሠሩትን በመመልከት ልምድ ለማለዋወጥ ጉብኝት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ተደጋግፎ በመሥራት እና ችግሮችን በጋራ በመፍታት የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በክልሉ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ከአማራ ክልል ውጪ ኾኖ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚለቀቀው መረጃ የከፋ ችግር ያለ ቢያስመስለውም በተጨባጭ ሲታይ ግን አመራሩ ችግርን በመቋቋም የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ”ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ የሚሠሩም አሉ” ያሉት ሚኒስትሯ ”ራሳችን ከየትኛው እንደኾንን አውቀን ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመልካም አሥተዳደር ችግር መቀረፍ፣ ለልማት ጠንክረን በመሥራት ለአካባቢያችን እና ለክልላችን መለወጥ መሥራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ የአማራ ክልል ሕዝብን ችግሮች ለመፍታት የከተማ አመራሩም ኀላፊነት ያለበት መኾኑን አውቆ እያንዳንዱ የየድርሻውን ኀላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። ”ከተሞች ላይ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መዋቅር በመዘርጋት እና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ብቻ አይፈቱም” ያሉት ሚኒስትሯ አመራሩ ሕዝቡን በማገልገል መንፈስ ሲሠራ ውጤታማ እንደሚኾን ተናግረዋል።

ሕዝብ እንዳይጉላላ አስቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ፤ የሚፈቱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችም ሕዝቡን የሚመጥኑ መኾናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ እና ሕዝቡን ለማገልገል እና ለመቀየር የተገኘውን የአመራርነት ዕድል እና አደራ በማወቅ ችግሮችን ለመፍታት ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅ ነው ሚኒስትሯ ያሳሰቡት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገራት በአዲስ አበባ አዳዲስ ኢምባሲያቸውን መክፈታቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አስፈላጊ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next article“በጎጃም ኮማንድ ፖስት ስር የሚገኘው ኮር የተሻለ ግዳጅ ለመፈጸም ራሱን ማዘጋጀት አለበት” ብርጋዴር ጀኔራል አዘዘው መኮንን