
አዲስ አበባ: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኾነው አዲስ የተሾሙት አቶ ነብዩ ተድላ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አዳዲስ ኢምባሲዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ቢሮ በአዲስ አበባ እየከፈቱ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ 134 ሀገራት ኢምባሲያቸውን በአዲስ አበባ መክፈታቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት ብቻ ኬፕቨርዲ እና አርሜኒያ አዲስ ኢምባሲ በአዲስ አበባ ከፍተዋል። ይህም አዲስ አበባን ታላቅ የዲፕሎማሲ መዲና ከማድረግ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ታላቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የ17 ሀገራት አዳዲስ እና ተተኪ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ አቅርበዋል ተብሏል።
የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዎ ካሲስ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የተለያዩ ምክክሮችን በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደላቀ ሁኔታ ለማሳደግ ተስማምተዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ የተደጋጋሚ ቀረጥን ማስቀረት የሚያስችል ስምምነትም ተፈራርመዋል። ስዊዘርላንድ 5ኛዋ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ መዳረሻ ሀገር መኾኗም በመግለጫው ተጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ በሳምንቱ ከተለያዩ ተቋማት እና ሀገራት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል ብለዋል። በሚቀጥለው ሳምንት የማልታ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!