
ጎንደር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) የሚመራው የፌዴራል የድጋፍ እና ሱፐርቪዥን ቡድን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ከተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በጎንደር ከተማ እየመከሩ ነው። ምክክሩ ባለፉት ወራት በተከናወኑ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች አፈጻጸም ዙሪያ ያተኮረ ነው።
ለውይይቱ መነሻ ጽሑፍ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የዞኑ መሬት መምሪያ ኀላፊ አላምረው አበራ የቀረበ ሲኾን ያጋጠመውን የሰላም እጦት በመቅረፍ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑ ተመላክቷል። የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በተለይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳድሮች ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የሕዝብ ውይይት መደረጉ ተነስቷል።
የቀረበው የውይይት መነሻ እንደሚያሳየው ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ወዲህ በድግግሞሽ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተሳተፉባቸው የሕዝብ ውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። በዚህም ማኅበረሰብ አቀፍ የሰላም ጥበቃ ሥራው የተሻለ ውጤት እያሳየ ስለመኾኑ ነው የተገለጸው። ከሰላም ግንባታ ጋር በተገናኘ መንግሥት ያቀረበውን ምሕረት ተከትሎ በዞኑ 1 ሺህ 558 ታጣቂወች በምሕረት ገብተው ሥልጠና ተሰጥቷቸው መደበኛ ሕይዎታቸውን እንዲመሩ መደረጉ ተነግሯል።
በውይይቱ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ እና በአረንጓዴ ልማት የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ቀርበዋል። በዞኑ በመኸር ወቅት የግብርና ሥራዎች 527 ሺህ 699 ሄክታር መሬት በተለያዩ አዝዕርቶች እንደተሸፈነ የተነገረ ሲኾን ከዚህም 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱ ተጠቅሷል።
በተያዘው ዓመት ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በዚህም 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኞች ለቀጣይ የክረምት ወራት ዝግጁ ኾነዋል ተብሏል። ችግኞቹ በ9 ሺህ 237 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲኾን በ764 ተፋሰሶች ይተከላሉ ተብሏል።
በምክክሩ ግብዓት በወቅቱ አለመቅረብ፣ የሰብል በሽታ ሲከሰት አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት፣ የኢንተርኔት አለመኖር፣ የንግድ እድሳት ለማድረግ እንቅፋት መፍጠሩ እና ለዞኑ ሕዝብ ፍጆታ የሚኾን የስኳር አቅርቦት እጥረት መኖር በውይይቱ በውስንነት የቀረቡ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው የተባሉ ጉዳዮች ናቸው።
ዘጋቢ:-ኃይሉ ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!