
ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት ከሕዳር 1/2016 ዓ.ም እስከ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል። ይሁን እንጅ በተለያዩ ምክንያቶች የቆጣሪ ውል እድሳቱን እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም ማራዘሙን አገልግሎቱ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
በአማራ ክልልም ከሕዳር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ በ135 የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እድሳት እየተደረገ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አሥኪያጅ ማተቤ ዓለሙ ገልጸዋል። በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በሥራው ላይ እንቅፋት ቢፈጥርም ከማኅበረሰቡ ጋር በመነጋገር የእድሳት አገልግሎቱ እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የእድሳት ጊዜው መራዘሙ በክልሉ በጸጥታ እና በተለያዩ ምክንያቶች ማሳደስ ያልቻሉ ደንበኞች እንዲያሳድሱ እድል ፈጥሯል ብለዋል። የቆጣሪ ውል የያዙ አምስት ዓመት እና ከዚያ በላይ የኾናቸው ደንበኞች የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ፣ የቀድሞ ውል እና ቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ ከኾኑ ደግሞ ካርድ የተሞላበትን ደረሰኝ በመያዝ ውል በገቡበት ወይም ቆጣሪ በተመዘገበበት አገልግሎት መሥጫ ማዕከል በመሔድ ወይም ሕጋዊ ውክልና በመያዝ ውላቸውን እንዲያሳድሱ አሳስበዋል፡፡ ማኅበረሰቡም እድሳቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የውል እድሳቱ ቆጣሪን ለማይታወቅ አካል የሚያስተላልፉ ደንበኞችን ለመቆጣጠር፣ የኃይል ሥርቆትን ለማስቀረት፣ የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለማቃለል፣ ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን፣ ተዓማኒነት እና ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት ለማስፈን ያስችላል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!