ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ዞን መግባቱ ተገለጸ፡፡

25

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን እንዳሉት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለ2016/17 የምርት ዘመን አገልግሎት የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ እየገባ ነው፡፡

ለዞኑ 1 ሚሊዮን 544 ሺህ 956 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ስለመፈጸሙ የተናገሩት መምሪያ ኀላፊው ይኽ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 502 ሺህ 316 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ገብቷል ብለዋል።
የዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡

መምሪያ ኀላፊው ቀሪው ማዳበሪያ በጊዜ እንዲቀርብ በየደረጃው ያለው አመራር እና ባለሙያ ጠንከር ያለ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል። በዚህ በጀት ዓመት ምንም አይነት የአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦት ችግር አይገጥምም ያሉት አቶ አበበ ወደ ዞኑ ከገባው ማዳበሪያ 376 ሺህ 176 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ መሠረታዊ ማኅበራት በማጓጓዝ 131 ሺህ 734 ኩንታል ማዳበሪያ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።

በዞኑ የመስኖ ልማትን ጨምሮ 149 ሺህ 846 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን የገለጽት ኀላፊው ስርጭቱ እንዲፋጠን በየደረጃው ያለው አመራር እና ባለሙያ ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው አርሶ አደሩ በየወረዳው በወጣለት የሥርጭት መርሐ ግብር መሠረት በየአካባቢው ካሉ መሠረታዊ ማኅበራት የአፈር ማዳበሪያ መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማዋን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።
Next articleበ135 የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የቆጣሪ ውል እድሳት እየተደረገ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።