እየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማዋን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።

22

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በግንባታ ላይ ያሉ መሠረተ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በፌዴራል መንግሥት እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶች የከተማውን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ በማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ተደርገው እየተሠሩ መኾኑን አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ እና በአማራ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ የሚሠራውን ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ ባይ ፓስ የመንገድ ግንባታ፣ ከእንጨት ወደ ኮንክሪት የሚቀየረውን የመብራት ገመድ ዝርጋታ እና የውኃ መሥመር ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በፌዴራል መንግሥት እየተሠሩ መኾናቸውን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ አፈጻጸማቸው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ማኅበረሰቡ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በማጽናት ሕዝብ እና መንግሥት ሙሉ ትኩረታቸው ልማት ላይ ብቻ መኾን እንደሚገባም አሳስበዋል። የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ሲሳይ አየለ በከተማ አሥተዳደሩ በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እና ከከተማው የውስጥ ገቢ 43 ፕሮጀክቶች ተለይተው በግንባታ ሂደት ላይ መኾናቸውን አብራርተዋል።

ከከተማው የውስጥ ገቢ በሚሰበሰብ 798 ሚሊዮን ብር በጀት የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው አስረድተዋል። የኮምቦልቻ ባይ ፓስ መንገድ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር ሚሊዮን ጌታቸው በበኩላቸው የተሠራው አማራጭ መንገድ ከሰባት ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ሲኖረው አራት ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተላለፍ የሚችል መኾኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀከቱ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲኾን ስድስት ድልድዮች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ በቦርከና ወንዝን ላይ የሚገነባው እና 80 ሜትር ርዝመት እና 21 ሜትር ስፋት ያለው ድልድይ በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን አብራርተዋል። መረጃው የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጽንፈኛው እና ዘራፊው ቡድን በፈጠረው ችግር ምክንያት በመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱ እና በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ገለጸ።
Next articleከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ዞን መግባቱ ተገለጸ፡፡