ጽንፈኛው እና ዘራፊው ቡድን በፈጠረው ችግር ምክንያት በመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱ እና በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ገለጸ።

109

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በተፈጠረው ችግር በአራት ዞኖች ብቻ በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ 110 ባለሀብቶች ላይ ውድመት መድረሱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ገልጸዋል። ቢሮ ኀላፊው እንደገለጹት ባለፉት ወራት በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በገጠር የወል መሬት ወረራ ተፈጽሟል።

በከተማ ዙሪያ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ደግሞ ሕገ ወጥ ግንባታ መስፋፋቱን ነው የገለጹት። ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያገለግሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ውድመት ድርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በዘመናዊ መንገድ የተጀመረውን የይዞታ ማረጋገጥ ተግባር በተቀመጠው ጊዜ እንዳይከናወን ኾኗል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከአበዳሪ ተቋማት የመሬት ይዞታውን ማረጋገጫ ደብተር በመጠቀም የብድር አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጓል ብለዋል። በገጠር መሬት ለሚነሱ የፍርድ ቤት ክርክሮች አጣርቶ ለፍትሕ አካላት ትክክለኛውን ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም፤ በዚህም ምክንያት በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው፡፡ በ10 ዞኖች ለሚገኙ 342 ባለሀብቶች የልማት አፈጻጸም ውጤት መሙላት አለመቻሉን አንስተዋል።

በሌላ መንገድ ዘራፊው እና ጽንፈኛው ቡድን በፈጠረው ችግር ምክንያት በሰሜን ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞኖች እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ 110 ባለሀብቶች ውድመት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው፡፡ በአትክልት፣ ፍራፍሬ እና ቡና ልማት ዘርፍ ለመሰማራት በክልሉ ኢንቨስትመንት በአዲስ ውል የወሰዱ 49 ባለሀብቶች ወደ ልማት አለመግባታቸውንም ገልጸዋል።

ጽንፈኛው እና ዘራፊው ቡድን በፈጠረው ችግር ምክንያት ብድር ለመበደር፣ ውል ለማራዘም እና ለማደስ፣ ፕሮጀክት ለመቀየር፣ ከልማት አፈጻጸም ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን ለመፈጸም በባለሀብቶች ላይ ከፍተኛ የኾነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አንስተዋል። ባለሀብቶች በገቢያ ትስስር ችግር ምክንያት ምርታቸውን ከቦታ ቦታ አዘዋውረው ለመሸጥ አልቻሉም፤ ይህም በክልሉ እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊውያን ጋር በመኾን ሀገረ መንግሥት እንዲፀና ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ያነሱት ኀላፊው ክልሉ አሁን ከገጠመው ችግር እንዲወጣ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል። በመገዳደል፣ ሰላም በመንሳት፣ በሁከት እና ብጥብጥ የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩን ያነሱት ኀላፊው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ መላው የክልሉ ሕዝብ ልክ እንደ ከዚህ በፊቱ ከፌዴራል እና ከክልሉ የፀጥታ መዋቅር ጎን በመሰለፍ የትናንቱን የታላቅነት ታሪኩን በድጋሚ እንዲያረጋግጥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢማን ኢስላሚክ አሶሴሽን” ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።
Next articleእየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማዋን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።