“ሀገር ያለ መንግሥት፣ መንግሥት ያለ ግብር ሕልውና የላቸውም” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ

69

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡በመግለጫቸውም በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በገቢ አሠባሠብ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

የኅብረተሰቡን የመልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ መፍታት እንዲያስችል የገቢዎች ቢሮ ከበፊቱ የተሻለ እቅድ በማቀድ ወደ ሥራ ገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የአማራ ክልል በሀገር ደረጃ ያለውን የምጣኔ ሀብት ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ታላቅ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ ባለው አስተዋጽዖ ልክ ገቢ መሠብሠብ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡ ገቢን በተገቢው መንገድ መሠብሠብ ካልተቻለ የሕዝብ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የማኀበራዊ አገልግሎት ጥያቄዎችን መመለስ እንደማይቻልም ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በክልሉ 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ እቅድ ይዘው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አስታውሰው፣ ክልሉ ካለው አቅም አንጻር የታቀደው እቅድ በቂ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ወደ ታክስ ክፍያ ያልገባውን የኅብረተሰብ ክፍል ታክስ እንዲከፍል የማድረግ ሥራ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

ክልሉ በስምንት ወራት 24 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብቻ መሠብሠቡን አንስተዋል፡፡ የተሠበሠበው ገቢ ያመቱን 34 በመቶ ብቻ መኾኑም ተመላክቷል፡፡ እቅዱ የክልሉን ሰላም እና መረጋጋትን ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በእቅዳቸው ልክ እንዳይፈጽሙ እንዳደረጋቸው ነው የተናገሩት፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተግባብቶ እና ሀሳብን ሽጦ የሚመለሱ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ነፍጥን አንስቶ የሚንቀሳቀሰው ኀይል በእቅዱ ልክ እንዳይሠራ አድርጓል ብለዋል፡፡ ነፍጥን ያነሳው ኀይል ሀሳብን በጦርነት ነው ማስፈጸም የምችለው ብሎ መነሳቱ የጽንፈኝነት መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የጽንፈኛ ተግባር እና አመለካከት ወደ ጦርነት ስላስገባ ክልሉ በችግር ውስጥ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ጥያቄዎችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ያምናል ያሉት ኀላፊው ከዚህ ውጭ ያሉ አካሄዶች እና የኀይል እርምጃዎች የሕዝብን አንጡራ ሀብት እያጠፉ ወደ ድህነት አዙሪት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው ብለዋል፡፡ ገቢን በበቂ ኹኔታ አለመሠብሠብ በክልሉ የትምህርት እና የጤና ግብዓቶችን ለማሟላት ተግዳሮት መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡

በዓመቱ መሠብሠብ የሚቻለውን ገቢ መሠብሠብ ካልተቻለ የክልሉን ሕዝብ ድህነት ለተጨማሪ ዓመት ማራዘም እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ በቀሪ ጊዜያት ያልተሠበሠበውን ገቢ ለመሠብሠብ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ጽንፈኛው ኀይል ግብር አትክፈሉ በማለት በመሪዎች እና በባለሙያዎች ከፍተኛ ጫና እያደረሰ እንዲኹም የገቢ ተቋማት ደግሞ የመቃጠል እና የመዘረፍ አደጋ እንደደረሰባቸው ነው የገለጹት፡፡ ገቢ እንዳይከፈል የማድረግ አካሄድ ክልሉን በእጅጉ እንደሚጎዳውም አመላክተዋል፡፡

ነገር ግን ዜጎች ግብርን በተገቢው መንገድ መክፈል እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። በገቢ ሥርዓቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡ በክልሉ የተሻለ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የተሻለ ግብር መሠብሠብ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩ ግብር ከፋዮች በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት ችግር እየተፈጠረባቸው መኾኑንም ነው ያሉት ቢሮ ኅላፊው፣ ጽንፈኛ ኀይሉ ኬላ በመዘርጋት ሕገ ወጥ ግብር እያስከፈለ ነውም ብለዋል፡፡

በክልሉ እየተፈጠረ ያለው አንጻራዊ ሰላም አርሶ አደሮች ግብር እንዲከፍሉ እያደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ሀገር ያለ መንግሥት፣ መንግሥት ያለ ግብር ሕልውና የላቸውም ብለዋል። ሀገር ቀጣይነት እንዲኖራት እና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንዲኖር ከተፈለገ የመንግሥት መኖር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የኀይል እርምጃዎች ወደ ኃላ ይመልሱ እንደኾነ እንጂ ለሀገር እድገት ቅንጣት ታክል አስተዋጽዖ እንደሌላቸው ነው ያመላከቱት፡፡

የሠለጠነ መንገድን መምረጥ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ የታክስ አሥተዳደር ሥርዓትን በማክበር ግብርን በታማኝነት ለሚከፍሉ ግብር ከፋዮችም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን በቅንነት እና በታማኝነት መክፈል እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በቀጣይ ጊዜያት የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮ ቴሌኮም ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአካል ድጋፍ እና የቴክኖሎጂ መርጃ መሣሪያዎችን ድጋፍ አደረገ።
Next article“ኢማን ኢስላሚክ አሶሴሽን” ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።