
አዲስ አበባ: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም የአካል ድጋፍ እና የቴክኖሎጂ መርጃ መሣሪያዎችን በመላዉ ሀገሪቱ ለሚገኙ 500 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል። የኢትዮ ቴሌኮም ተወካይ መሳይ ውብሸት የዜጎች ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ ተቋማቸው ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ የዊልቸር፣ ክራንች፣ ነጭ በትር እና የጆሮ አጋዥ ማዳመጫዎች ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ቢኖሩም የአካል እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ተጠቃሚ የኾኑት 1 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው ብለዋል። ድጋፉ የነበረባቸውን ችግር የሚያቃልል መኾኑን የገለጹት ድጋፉ የተደረገላቸው ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው በድጋፉ መደሰታቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከሰጠው 500 አካል ጉዳተኛ ድጋፎች ውስጥ 199 በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች በዛሬው ዕለት የተበረከተ ሲኾን ቀሪዎቹ ደግሞ ለሁሉም ክልሎች ተደራሽ ይደረጋሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!