“ደብረ ማርቆስን ጨምሮ አምስት ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባን ነው” የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

40

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አምስት ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መኾኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየሠራ ነው።

የሚያበራቸውን አውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አየር መንገዱ 136 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸዋል። አየር መንገዱ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አምስት የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ኤርፖርቶቹ የሚገነቡት ሚዛን ቴፒ አማን፣ ነጌሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱና ደብረ ማርቆስ መኾናቸውን ገልጸው፤ አራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል። ይህም በሀገር ውስጥ ያሉ ደንበኞች ፍላጎትን ተከትሎ የሚተገበር ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች መዳረሻዎች ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ ግንባታ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ጉዳት የደረሰባቸው የአክሱምና የቀብሪደሃር ኤርፖርቶች እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። ኢዜአ እንደዘገበው አየር መንገዱ በቀጣይም የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፀጥታ ችግሮችን ለመቀልበስ እና ሰላምን ለማጽናት የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።
Next articleኢትዮ ቴሌኮም ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአካል ድጋፍ እና የቴክኖሎጂ መርጃ መሣሪያዎችን ድጋፍ አደረገ።