የፀጥታ ችግሮችን ለመቀልበስ እና ሰላምን ለማጽናት የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።

52

ደባርቅ: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፌዴራል መንግሥት የድጋፍ እና ሱፐርቪዥን ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የተከናዎኑ ተግባራትን እየገመገመ ነው፡፡ በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) የሚመራው የፌዴራል መንግሥት የድጋፍ እና ሱፐርቪዥን ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የተከናዎኑ ተግባራትን እየገመገመ ነው፡፡

ቡድኑ በዞኑ ሰላምን ለማስፈን እና ልማትን ለማስቀጠል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ይመለከታል። መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች ላይም ከዞኑ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል። በውይይቱ ላይ የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ በዞኑ የተከናወኑ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርቱም ዞናዊ የፀጥታ ችግሮችን ለመቀልበስ እና ሰላምን ለማጽናት የተለያዩ ተግባራት መከናዎናቸው ተገልጿል። ሕዝባዊ ውይይቶችን፣ የአመራር ሥልጠና፣ የፀጥታ ኃይሎችን ማሠልጠን፣ የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለገቡ አካላት የተሃድሶ ሥልጠና መሥጠት እና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸው ተነስቷል።

በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች መንግሥት ሕግን እንዲያስከብር እና የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ማኅበረሰቡ ጥያቄ ማቅረቡ ተገልጿል። በዞኑ የሚታየው አንጻራዊ ሰላም የተሠራው ሥራ ውጤት መኾኑ እና በፀጥታ ችግር ተቋርጠው የነበሩ የልማት ሥራዎች መቀጠል መቻላቸው አበረታች ነው ተብሏል። በጦርነት የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩን ማኅበረሰቡ እንዲረዳ እና ሰላሙን እንዲጠብቅ መደረጉም ነው የተገለጸው።

አቶ ቢምረው ዞኑ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅሞ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የግብርና ግብዓት ሥርጭት፣ የበጋ መስኖ እና የመኸር እርሻ ወራት የግብርና ሥራዎች፣ በቱሪዝም፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ የመንግሥት ግብር የመሰብሰብ እና ሌሎች ተግባራቶች እየተከናወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በዞኑ ከበለስ መካነ ብርሃን ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ውጭ በፌዴራል እና በክልል መንግሥት በርካታ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ተጀምረው በሰሜኑ ጦርነት እንደተቋረጡ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ድረስ ወደ ሥራ አለመግባታቸው በማኅበረሰቡ የእለት ከእለት ተግባራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸው ተገልጿል።

የመንገድ መሠረተ ልማት ወደ ሥራ አለመግባት እና ሰፊ ኢንዱስትሪ መንደር አለመኖር በዞኑ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ያነሱት ምክትል አስተዳዳሪው የፌዴራሉ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የሕዝብ ጥያቄ ነው በሚል አንስተዋል፡፡ አዳርቃይ ሆስፒታልን ጨምሮ በዞኑ በጦርነት የወደሙ ተቋማት ላይ በሚፈለገው ልክ መልሶ ግንባታ ሥራ ባለመሠራቱ በማኅበረሰቡ ጤና ላይ ተጽእኖ አሳድረዋል ብለዋል። የድጋፍ እና ሱፐርቪዥን ቡድኑ የዞኑን ሰላም ለማጽናት የተሠራው ሥራ እና ዞኑ የሚገኝበትን ሰላማዊ ሁኔታ አድንቋል።

ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም የትውልድ እና የፖለቲካ ባሕል ግንባታን ይፈልጋል” አቶ አብዱ ሁሴን
Next article“ደብረ ማርቆስን ጨምሮ አምስት ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባን ነው” የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው