
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን ከደሴ ከተማ ከግል እና ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከተውጣጡ መምህራን ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ የአማራ ክልልን የገጠሙት የሰላም፣ የጸጥታ እና የደኅንነት ችግሮች ስለመኖራቸው አውስተዋል፡፡ ሕዝቡ በየደረጃቸው የሚያነሳቸው የተፈቱም ያልተፈቱም ፍላጎቶች ስለመኖራቸው አንስተዋል፡፡
ችግሮችን በሰላማዊ መንግድ መፍታት ካልተቻለ ትውልድ ተሻጋሪ አዙሪት ውስጥ ያሰገባል ነው ያሉት። እስካኹንም የተለያዩ የሕዝብ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላም የመንግሥት እና የሕዝብ መስተጋብር ውጤት እንደኾነም አንስተዋል፡፡
ሰላም እንዲሰፍን ትውልዱ ላይ የእሴት እና የሥነ ምግባር ግንባታ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ ለዚህ ግንባታ ወሳኝ ከኾኑት መካከል የትምህርት ተቋማት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡ ተቋማቱን ከሚመሩ እና ከሚያስተባሩ አካት ጋር የሚደረግ ውይይት ሰላምን በዘላቂነት ከማጽናት ባሻገር የትውልድ እሴትን፣ ሥነ ምግባርን እና የሀገር ሉአላዊነትን ገንብቶ የሚገጥሙ ችግሮችን በሰከነ ውይይት እና ምክክር ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
“ሰላም የትውልድ እና የፖለቲካ ባሕል ግንባታን ይፈልጋል” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተግባሩ የሚከናወነው በተማረ እና በሠለጠነ የሰው ሀይል በመኾኑ መምህራን ልዩ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡ መምህራን የተጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!