
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ 7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬዎች በኩታ ገጠም እየለማ ይገኛል።
ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ እና አፕልም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በስፋት እየለሙ ከሚገኙ የአትክልት እና ፍራፍሬዎች መካከል ይገኙበታል። የቡና ምርትን ብቻ በየዓመቱ ከ1ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው የአርሶ አደሮችን የገቢ አማራጭ ለማስፋት በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በቀጣዮቹ የክረምት ወራት ከ2 ሚሊዮን በላይ ቋሚ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅትም መደረጉንም አንስተዋል።
የዘንድሮው የችግኝ ዝግጅት ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በስፋት በሚታወቅባቸው የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬዎችን እንዲኹም በሌሎችም ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ከችግኝ ዝግጅት ጎን ለጎን የተከላ ቦታዎችን የመለየት እና ይዞታቸውን የማስከበር ሥራ ከወዲሁ እየተሠራ መኾኑንም ምክትል መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። የችግኝ ዝግጅቱ 15 በሚኾኑ የመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች እየተከናወነ እንዳለም ለማወቅ ተችሏል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!