
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በቀጣናው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ እና የኮማንድ ፖስቱን የሥራ አፈጻጸም በዛሬው እለት ገምግሟል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በቀጣናው የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት የፀጥታ እና የመንግሥት አሥተዳደር አካላት በቅንጅት መሥራታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
አሁንም በቀበሌ ደረጃ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለማስተካከል ኅብረተሰቡም ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባም ዶክተር አሕመዲን አሳስበዋል። የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በጋራ መፍትሔ በመስጠት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ ይገባል ያሉት ደግሞ የኮማንዶ እና አየር ወለድ እዝ ዋና አዛዥ እና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ናቸው።
አካባቢው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲቆይ ፍላጎት የለም ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ ይህ እንዲሳካ ግን የፀጥታ እና የመንግሥት የአሥተዳደር አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን አሁን ላይ የተሻለ የሰላም አየር አለ ያሉት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ ኅብረተሰቡ ባልተገባ ማደናገሪያ ከልማት ሥራው ወደኋላ እንዳይል አሳስበዋል።
ወቅቱ ለመኸር እርሻ ዝግጅት የሚደረግበት እንደመኾኑ የግብዓት አቅርቦት እና መሰል ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸትም ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ የተሻለ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!